መንግስት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡- ዶክተር ለገሰ ቱሉ

10 Days Ago
መንግስት ለኅብረ-ብሔራዊ  አንድነት መጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፡- ዶክተር ለገሰ ቱሉ
መንግስት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መጠናከር እና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ገለጹ።
 
በኢትዮጵያ ለዘመናት ስር ሰደው የቆዩና ያለመግባባት መነሻ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት መንግስት በርካታ የሪፎርም እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ዶክተር ለገሰ ገልጸዋል።
 
ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ መንግስት በፅኑ ይሰራል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የተፈጸሙ በደሎችን በእርቅ በይቅርታ እና በፍትሕ ለመሻገርም የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁን አንስተዋል።
 
በሀገራዊ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርም ህዝብ በአጀንዳዎቹ ላይ ምክክር አድርጎ መፍትሔ የሚያቀርብበት ሀገራዊ ምክክር ለማካሄድ የዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
 
መንግስት ኢትዮጵያዊ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት ልዩ ትኩረት መስጠቱን በማንሳት፤ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
 
የኢትዮጵያን አንድነት ለማፅናትና የህዝቦችን የዘመናት አብሮነት በጠንካራ መሰረት ለማዝለቅ አሰባሳቢ ትርክት ሚናው የላቀ እንደሆነም ሚኒስትሩ አንስተዋል።
 
ለዚህም መንግስት በብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ አሰባሳቢ የጋራ ትርክትን መገንባት ላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
 
የጋራ ትርክቱ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯን ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የህዝቡን አንድነት ለማጎልበት ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
 
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመንግስት መረጃዎች ሳይፋለሱ ወቅታቸውን ጠብቀው ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
 
የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር እንዲሁም ህብረተሰቡ ለልማት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተመሳሳይ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ ላይ እየሰራ ነውም ብለዋል።
 
የተዛቡ መረጃዎችን መመከት፣ልዩነትን የሚያባብሱ አስተሳሰቦችን ማረቅ እና የህብረተሰቡን የአብሮነት እሴት ለሚያጎለብቱ ስራዎች ትኩረት ተሰጥቷል ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው።
 
በቀጣይም የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ አሰባሳቢ ትርክትና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን በተቀናጀ መልኩ ተደራሽ የማድረጉ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር ለገሰ አስረድተዋል።
 
 
 
 
 
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top