ከመኖሪያ ቤት እስከ 20 ሜትር ድረስ ያለውን ስፍራ የማፅዳት እና የማልማት ግዴታ የነዋሪዎች እንደሆነ ያውቃሉ?

10 Days Ago
ከመኖሪያ ቤት እስከ 20 ሜትር ድረስ ያለውን ስፍራ የማፅዳት እና የማልማት ግዴታ የነዋሪዎች እንደሆነ ያውቃሉ?
በአዲስ አበባ የ90 ቀናት እና 60 ቀናት በርካታ የልማት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ገልጿል፡፡
 
የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ቻይና ግቢ ብሎክ ነዋሪዎች ሰፈራቸው ለኑሮ ምቹ ያልነበረ ቢሆንም፤ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመነጋገር ሰፈራቸውን ውብ እና ማራኪ ማድረግ ችለዋል።
 
የአካባቢው ነዋሪ እና የኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አሳምነው ይልማ ለኢቢሲ ሳይበር እንደገለጹት፤ በአካባቢያቸው ላለፉት ዓመታት የፍሳሽ ማስወገጃ እና የአረንጓዴ ልማት እንዳልነበር ይናገራሉ፡፡
 
በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ይቸገሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አሳምነው፤ ህብረተሰቡን በማስተባበር አካባቢውን ማልማት ስለመቻሉ ይገልጻሉ።
 
ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሔለን ተመስገን፤ በሳምንት ሁለት ጊዜ ቆሻሻ እንደሚወገድላቸው እንዲሁም የቆሻሻ መጣያ ችግር እንዳይኖር የቆሻሻ ማጠራቀሚያ በማስቀመጥ አካባቢውን ፅዱ ለማድረግ መሰራቱን ተናግረዋል።
 
የመኖሪያ አካባቢን ለማልማት እና ማራኪ ለማድረግ የራስ ተነሣሽነት በቂ ነው የሚሉት ወ/ሮ ሔለን፤ “በሰራነው ስራ ለልጆች መጫወቻ እንዲሁም ለኑሮ ምቹ ስፍራ ፈጥረናል” ብለዋል።
 
የአካባቢው ፅዳት ለኑሮ ምቹ ከመሆኑም ባለፈ፤ ለበርካታ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ቀረፃ ማከናወኛ ተመራጭ ስፍራ እንዲሆን እዳስቻለው ተነገሯል።
 
በማህበረሰቡ ተነሳሽነት የሚሰሩ የአካባቢ ማስዋብ ስራዎች ተገቢ ናቸው የሚለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፤ በከተማዋ በ90 እና ብ60 ቀናት የሚሰሩ ስራዎች መኖራቸውን ገልጿል።
 
በከተማዋ ደንብ መሰረት ማንኛውም የከተማው ነዋሪ ከመኖሪያ ቤት እስከ 20 ሜትር ስፋት ውስጥ ያለን ስፍራ የማጽዳት እና የማልማት ግዴታ እንዳለበት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ለማ (ዶ/ር) አመላክተዋል፡፡
 
የአረንጓዴ ልማት ስራዎች በከተማዋ በራካታ አካባቢዎች እየተሰሩ ቢሆንም፤ ቦሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እና የካ ክፍለ ከተሞች የተሻለ ስራ የተሰራባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
 
እነ አቶ አሳምነው ይልማ እና ወ/ሮ ሔለን ተመስገን አካባቢያቸውን እዳለሙት ሁሉ በተለያዩ የክፍለ ከተሞች ከ42 በላይ ብሎኮች ተመሳሳይ ልማት እንደተካሄደባቸው እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
 
በሜሮን ንብረት

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top