ከየመን ወደ ጂቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በደረሰባት የመገልበጥ አደጋ 16 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው አለፈ

8 Mons Ago 880
ከየመን ወደ ጂቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በደረሰባት የመገልበጥ አደጋ 16 ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸው አለፈ

ትላንት ምሽት ከየመን የባህር ዳርቻ ልዩ ስሙ አራ ከሚባል ስፍራ 77 ኢትዮጵያውያን ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ ጅቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ጎዶሪያ በሚባል አካባቢ በደረሰባት የመገልበጥ አደጋ የ16 ኢትዮጵያውያን ሕይወት አልፏል፡፡

በጀልባ መገልበጥ አደጋው የ16 ኢትዮጵያውያን ሕይወት ሲጠፋ አብረው የተሳፈሩ 28 ዜጎችን እስካሁን ማግኘት አለመቻሉ ተጠቅሷል፡፡

በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል 5ቱ ሕፃናት መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን፤ 1 ሴትን ጨምሮ 33 ፍልሰተኞች በሕይወት ተርፈው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል።

ኤምባሲው በደረሰው አሳዛኝ ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልፆ፤ ከጅቡቲ ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት የሚደረገው ህገ ወጥ ጉዞ እጅግ አደገኛ ከመሆኑም በላይ በየጊዜው የዜጎቻችንን ሕይወት እያሳጠ እንደሚገኝ አስገንዝቧል።

ዜጎች በህገ ወጥ ደላሎች የሀሰት ስብከት በመታለል ውድ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው በዚህ አደገኛ የጉዞ መስመር ከመንቀሳቀስ እንዲቆጠቡ ያሳሰበው ኤምባሲው፤ የፍትህ አካላትም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ከገጠራማ የአገሪቱ አካባቢዎች ዜጎችን በመመልመል ለስደት በሚዳርጓቸው ግለሰቦች ላይ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪውን አስተላልፏል።

ከ2 ሳምንት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በደረሰ አደጋ የ38 ፍልሰተኛ ዜጎቻችን ሕይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top