37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ

11 Mons Ago 1528
37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ተጠናቀቀ
ላለፉት ሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ማለዳ በተካሄደ የመዝጊያ ሥነ-ሥርአት ተጠናቅቋል።
 
አዲሱ የኅብረቱ ሊቀመንበር የሞሪታንያው ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ኡልድ ጋዙዋኒ በጉባኤው መዝጊያ ሥነ-ሥርአት ላይ ባደረጉት ንግግር ባለፉት 2 ቀናት በተካሄደው ጉባኤ የመጀመሪያውን 10 ዓመታት ያጠናቀቀውን አጀንዳ 2063 በመገምገም እና በቀጣይ 10 ዓመታት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ስራዎች በመለየት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
 
በአጀንዳ 2063 ሁለተኛው ምእራፍ የአፍሪካ የትምህርት ስርአት ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን ቅድሚያ በመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ኡልድ ጋዙዋኒ ጠቁመዋል።
 
አፍሪካ በተባበሩት መንግስት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ አግኝታ በዓለም የፀጥታ ጉዳዮች ላይ የራሷን አስተዋፅኦ እንድታበረክት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው የገለፁት።
 
እንደ ሊቀመንበሩ ገለፃ ሁላችንም የምንመኛትን ሰላም እና መረጋጋት ያለባት፣ ሰብአዊ መብት የሚከበርባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት እና የበለፀገች አፍሪካ ለመፍጠር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
 
አፍሪካ የራሷን እድል በራሷ እንድትወስን የሚሰራው ስራ አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ሊቀመንበሩ አፍሪካ የራሷን ችግሮች እና የውስጥ ፈተናዎቿን በራሷ ተቋማት በኩል ያለጣልቃ ገብነት ለመፍታት መስራት እንደሚገባም አንስተዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top