እንግሊዝ በሀገሯ የሚገኙ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዘዋወር የነደፈችው ረቂቅ ሕግ ፀደቀ

8 Mons Ago 822
እንግሊዝ በሀገሯ የሚገኙ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለማዘዋወር የነደፈችው ረቂቅ ሕግ ፀደቀ

እንግሊዝ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ ለማዘዋወር የነደፈችው እና ከፍ ያለ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የታመነው ረቂቅ ሕግ በሃገሪቱ ፓርላማ መጽደቁ ተሰምቷል።

ለሁለት ዓመታት ክርክር ሲደረግበት የቆየው ይህ ውሳኔ በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚስቴር ሪሺ ሱናክ እና በሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ መካከል የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የተደረሰ መሆኑ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ውሳኔው የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከእንግሊዝ ወደ ሩዋንዳ የሚያዘዋውር ሲሆን ስደተኞቹም የጥገኝነት ጥያቄያቸው እስከሚጠናቀቅ ድረስ በሩዋንዳ እንደሚቆዩ ነው የተጠቀሰው፡፡

ለሚቀጥሉት 664 ቀናት ስደተኞችን የያዙ አውሮፕላኖች ወደ ሩዋንዳ መብረር እንደሚጀምሩ የተገለፀ ሲሆን፤ በእቅዱ መሰረት 52 ሺህ የሚደርሱ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ ሩዋንዳ እንደሚዘዋወሩ ተጠቅሷል፡፡

"የሩዋንዳ ዕቅድ" የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ይህ ረቂቅ ህግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከእንግሊዝ ፓርላማ አባላት እና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ቢገጥመውም፤ የሃገሪቱ ፓርላማ እቅዱን ማፅደቁን ተከትሎ ህግ ሆኖ ሊወጣ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የዕቅዱ ተቃዋሚዎች ስደተኞቹን በኃይል ከአገር የማስወጣቱን ውጥን ማገድ የሚችል አዲስ የሕግ መቋቋሚያ ለማበጀት የሚያደረጉትን ጥረት አሁንም እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን የዘገበው ቢቢሲ ነው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top