የሰላም መልዕክተኛዋ የአፍሪካ ኩራት፡- ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ

9 Mons Ago 1260
የሰላም መልዕክተኛዋ የአፍሪካ ኩራት፡- ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ

ከዛሬ 32 ዓመት በፊት በዓለም አደባባይ ነግሣ ኢትዮጵያን እና አፍሪካን ያኮራች የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት አትሌት፡፡  

ሥራዋን አክባሪ፣ ታታሪ፣ ቅን፣ የመርህ ሰው፣ ሰውን አክባሪ የሚሉት መግለጫዎች ያንሷታል።

‘ሴት ልጅ አንገቷን ደፍታ፣ ቤተሰቦቿ የመረጡላትን ትዳር ይዛ መኖር አለባት’ የሚለውን የኖረ የሀገራችን አባባል ሰብራ ወደ አትሌትክሱ ዓለም በመቀላቀል ሌላ የህይወት መንገድ መኖሩን ያሳየች ብርቱ ነች።

በባርሴሎና ስታሸንፍ ደቡብ አፍሪካ በአፓርታይድ ምክንያት ከስፖርት ተገልላ ከቆየች በኋላ በኦሎምፒክ ያሳተፈቻትን አትሌቷን ኤለና ሜየርን ፈልጋ አብራ ደስታዋን ገለጸች፡፡ ያ ሁኔታም የደቡብ አፍሪካን እና የዓለም ሕዝብን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ ይህ ክስተት አርቆ አሳቢዋ ደራርቱ አብሮነትን መርህ ያደረገውን ስፖርትን የገለጸችበት ነበር፡፡ በዚህም በሚሊዮን ደቡብ አፍሪካውያን ልብ ውስጥ ተጽፋ እንደቀረች በየመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ስለ እሷ የጻፉአቸው ጽሁፎች ምስክሮች ናቸው፡፡

የዓለም አትለቲክስ ፌዴሬሽን እ.አ.አ በ2020 በባርሴሎና በተከበረው ዓለም አቀፍ የሰላም ቀንን አስመልክቶ በገጹ ባወጣው ጽሁፍ "የኦሎምፒክ ሜዳልያ ተሸላሚዎች ደራርቱ ቱሉ እና ኤለና ሜየር የ1992 የባርሴሎና ኦሎምፒክ ሲያሸንፉ የቀለም ልዩነት ሳይወስናቸው ‘እኛ አፍሪካውያን ነን’ በማለት በጋራ ተደስተዋል" ብሏል።

ሁለቱ አትሌቶችም ከ30 ዓመት በኋላ በባርሴሎና ተገናኝተው የዓለም የሰላም ቀንን እና አፍሪካዊ ድላቸውን በጋራ አስበዋል፡፡

ደራርቱ በ37 አመቷም የኒውዮርክ ማራቶንን ማሸነፍ የቻለች ምርጥ እና ፋና ወጊ አትሌት ነች።

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የተወለደችው 1965 ዓ.ም የምርጥ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው የአርሲዋ በቆጂ ነው፡፡

የሩጫ ውድድር የጀመረችው በትምህርት ቤት ውስጥ በ15 ዓመቷ ነው። ለዚህም እረኛ መሆኗ እና ለቤተሰቦቿ እና ጎረቤቶቿ በፍጥነት መላላኳ እንደጠቀማት ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ገልጻለች፡፡ ከሩጫ ጎን ለጎን ደግሞ ፈረስ መጋለብ ትወድ ነበር።

በትምህርት ቤት በውስጥ ፉክክር የጀመረችውን ሩጫ ትምህርት ቤቷን በመወከል ለወረዳ፣ ለአውራጃ ከዚያም ለክፍለ አገር መወዳደር ጀመረች።

ደራርቱ ቱሉ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ከነገሠች 32 ዓመታት አለፉት፡፡ በባርሴሎና ኦሎምፒክ በአስደናቂ አጨራረስ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት ነች። በዚህም ሻምበል አበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት የለኮሰውን የድል ችቦ ተረከበች፡፡

ፍልቅልቋ ደራርቱ በሩጫው ሜዳ ብቻ ሳትወሰን የአትሌትክስ ዘርፉን በመምራት፣ በማኅበራዊ ጉዳይ ተሳትፎዎቿ፣ በአስታራቂነቷ፣ ለሁሉም ባላት እኩል አመለካከቷ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለች ዕንቁ ነች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት፣ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እና በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንግረስ ደግሞ ኢትዮጵያን ወክላ የምክር ቤቱ አባል በመሆን ሀገሯን እና አፍሪካን ያኮራችበትን የአትሌትክስ ዘርፍ እየመራች ትገኛለች፡፡

በአመራሯም በ18ኛው የኦሪገኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም አሜሪካን ተከትላ በ2ኛነት፣ ከአፍሪካ ደግሞ በ1ኛነት እንድታጠናቅቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። በቶኪዮ ኦሎምፒክም አትሌትክሱን ሊያነቃቃ የሚችል ውጤት አስገኝታለች፡፡ ተተኪዎችን በማፍራት ረገድም የላቀ አመራር እየሰጠች ትገኛለች፡፡ ለዚህም በ13ኛው መላ አፍሪካ ጨዋታዎች የተመዘገበው ውጤት ማሳያ ሲሆን፣ ይህም ለቀጣዩ የ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ተስፋ የሚያሰንቅ ውጤትም ነው፡፡ የሩጫውን ድካም የምታውቀው ደራርቱ አመራር ስትሰጥ ቢሮ ተቀምጣ ሳይሆን ከአትሌቶች ጋር በሜዳ ተገኝታ ልምምድ በመሥራት፣ በውድድር ሜዳም ተገኝታ በማበረታታት ነው፡፡

እ.አ.አ በ1992 በተደረገው የባርሴሎና ኦሎምፒክ ክስተት በመሆን ከሀገሯ እና ከዓለም ሕዝብ ጋር ያስተዋወቃት ይህ ድል፣ የአንድ ሰው ድል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ሴቶች ሁሉ ድል ስለሆነ ልዩ ትርጉም እንዳለው ትገልጻለች፡፡

ብዙዎቹ ደራርቱ ከአትሌቲክሱ ርቃለች ብለው ከደመደሙ በኋላ በ1993 ዓ.ም በሲድኒ ኦሎምፒክ በአስደናቂ ሁኔታ በ10ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳለያ አሸናፊ ሆና እጅን በአፍ አስጭናለች።

ኢትዮጵያን ወክላ በተወዳደረችባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሁለት የወርቅ እና አንድ የነሀስ የኦሎምፒክ ሜዳሊያዎችን፣ አንድ የወርቅ እና አንድ የብር ሜዳሊያዎችን በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ በሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሦስት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገሯ አበርክታለች።

በአጠቃላይ ባደረገቻቸው ውድድሮች ደግሞ 16 ጊዜ በአንደኛነት ስታጠናቅቅ፣ አንድ ጊዜ ሁለተኛ፣ አንድ ጊዜ ሦስተኛ እንዲሁም ሁለት ጊዜ አራተኛ ሆና አጠናቅቃለች፡፡

እሷ የከፈተችው መንገድም ለብዙ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ማበረታቻ ሆኖ ሀገራችንን ያኮሩ ድንቅ አትሌቶችን ለማየት በቅተናል፡፡

ደራርቱ ወደ ኢንቨስትመንቱም ተቀላቅላ ላቧን ጠብ አድርጋ ባመጣችው ገንዘብ ለብዙዎች የሥራ ዕድልን ፍጥራለች፡፡ ለዚህም አሰላ፣ አዳማ እና አዲስ አበባ ምሥክሮች ናቸው፡፡

በተጨማሪም የሀገሯ ሰላምም ስለሚያሳስባት ሁሉም ችግሩን በነግግር እንዲፈታ በእንባ ጭምር ተማጽናለች፡፡ ለማንም ሳትወግን ሁሉም ቁጭ ብሎ ለሀገር ሰላም እንዲሠራ የምትችለውን ሞክራለች፡፡ ከኢትዮጵያ በላይ ምንም ነገር እንደሌለም በቃልም በተግባርም አስመስክራለች፡፡

በስኬቶቿም ብዙ የክብር ሽልማቶችን ተቀብላለች፡፡ ከነዚህም መካከል፡- የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተሬት ሰጥቷታል፡፡ ከደቡብ አፍሪካው ዌስተርን ኬፕታውን ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክትሬት አግኝታለች፡፡ በጣልያን በተካሄደ ዓለም አቀፍ ሽልማት የህይወት ዘመን የስፖርታዊ ጨዋነት ዘርፍ ተሸላሚ ነች፡፡ በአዳማ የሚገኘው ትልቁ አደባባይ በኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ተሰይሟል። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የሀያት አደባባይ በስሟ ተሰይሟል። የኢትዮጵያ የክብር ኒሻን ተሸልማለች። የ2014 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊ ነች፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top