በጣም አስፈሪ ለነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ክትባት መገኘቱ ከማዕከሉ ስኬቶች መካከል አንዱ ነው - የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ጂን ካሲያ

9 Mons Ago 1360
በጣም አስፈሪ ለነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ክትባት መገኘቱ ከማዕከሉ ስኬቶች መካከል አንዱ ነው - የአፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ጂን ካሲያ

የአፍሪካ በሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል በጣም አስፈሪ ለነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ክትባት ማግኘቱ ከማዕከሉ ስኬቶች አንዱ መሆኑን የአፍሪካ ሲዲሲ ዋና ዳይሬክተር ጂን ካሲያ ገለፁ፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ጂን ካሲያ ማዕከሉ እየሰራቸው ባሉት ሥራዎች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም፤ ማዕከሉ በአህጉሩ ሊከሰቱ ለሚችሉ ወረርሽኞች እና ሌሎች በሽታዎች መረጃን መሰረት በማድረግ የመከላከል እና ሲከሰቱም ፈጣን ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ተደራሽነቱን ለማሻሻል በጨረታ እና በግዢ ምክንያት የሚባክነውን ጊዜ እና ገንዘብ ለመቆጠብ መድኃኒቶች እና ክትባቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ እየሰራ መሆኑና በዚህም ውጤታማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ወባ፣ ኮሌራ፣ ኢቦላ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ሌሎች ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በጣም አስፈሪ ለነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ ክትባት መገኘቱ ከማዕከሉ ስኬቶች አንዱ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይም የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የተሻለ አግልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ ኮሌራ ያሉ በሽታዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየተስፋፉ መሆኑን እና ይህን ለመቋቋምም ስትራቴጂክ ዕቅድ አውጥተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ አሁን ባለው አቅሙ ዓለማውን ማሳካት እንደሚከብደው እና ሕብረቱ ገንዘብ እንዲለቅለት በዚህ ጉባኤ ላይ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡

እ.አ.አ በ2016 ተመሥርቶ ጥር 2017 ሥራውን የጀመረው ተቋሙ በዚህ ዕድሜው ስኬታማ ሥራዎችን መሥራቱንም ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ሲዲሲ የአባል ሀገራት የህዝብ ጤና ተነሳሽነቶችን ለመደገፍ እና የህዝብ ጤና ተቋሞቻቸው የበሽታ አደጋዎችን በፍጥነት እና በብቃት የመለየት፣ የመከላከል፣ የመቆጣጠር እና ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማጠናከር የተቋቋመ የአፍሪካ ህብረት ልዩ የቴክኒክ ተቋም እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top