የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የፓኪስታን ባለሐብቶች ልዑካን ቡድን እየተወያዩ ነው
***************************
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና የፓኪስታን ባለሃብቶች የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ምቹ ሁኔታዎች ላይ እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ፣ የሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የፓኪስታን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ልዑካን ቡድን አባላት፣ የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ተወካዮችንና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር እንዳሉት፤ ሁለቱ ሀገራት መልካም የሆነ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው።
የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉ በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራቱ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ፣ በሠላም ማስከበር፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መከላከል እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከፓኪስታን ጋር በትብብር መስራቱን እንደሚያጠናክርም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሻዛብ አባስ በበኩላቸው፤ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የዚሁ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
በግብርና ዘርፍ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በመስኖ ልማት፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎችም በጋራ መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኢዜአ ዘግቧል።
የፓኪስታን ንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ሰባ አንድ አባላትን አካትቶ ትላንት ማምሻውን አዲስ አበባ መግባቱ ይታወቃል።