ላለፈው 1 ዓመት የአፍሪካ ህብረትን የመሩት የሴኔጋሉ ፕሬዚደንት ማኪ ሳል ስልጣናቸውን ለአዲሱ ተሿሚ የኮሞሮሱ ፕሬዚደንት አዛሊ አሱማኒ አስረክበዋል።
ማኪ ሳል በርክክቡ ወቅት አዲሱ የህብረቱ ሊቀመንበር መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተው ይህን አህጉራዊ ሃላፊነት በብቃት እንደሚወጡ እርግጠኞች ነን ብለዋል።
አዲሱ ሊቀመንበር የስልጣን ርክክብ ባደረጉበት ወቅት የአፍሪካ ህብረት በቅርቡ በርዕደ መሬት አደጋ በርካታ ዜጎችን ላጡት ቱርክ እና ሶሪያ ትልቅ ሃዘን እንደተሰማው ገልጸዋል።
አዛሊ አሱማኒ በንግግራቸው እንዳሉት የማኪ ሳልን እንዲሁም የቀደሙ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበሮችን ፈለግ በመከተል ባለኝ አቅም ሁሉ ህብረቱን አገለግላለሁ ብለዋል።
አያይዘውም አህጉራችን አፍሪካ ከኮቪድ 19 ድቀት ሳትወጣ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እንደተጫናት ገልጸው፤ በኢኮኖሚው ዘርፍ መነቃቃትን ለመፍጠር ከአጋር አካላት ጋር ስራዎችን ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል።
አህጉሪቱ በወሳኝ መሰረተ ልማቶች ረገድ ያለባትን እጥረትም ማሟላት ሌላው የቤት ስራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አጀንዳ 2063 ተግባራዊ ማድረግ ላይም በትኩረት እንደሚሰሩ የኮሞሮሱ ፕሬዚደንት አዛሊ አሱማኒ ገልጸዋል።