አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለማቃለል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍና ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል - ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

5 Mons Ago
አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለማቃለል ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍና ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል - ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ

ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የመከላከል ሪፖርት አፈጻጸም ላይ ምክክር ተካሂዷል። 

የመድረኩ ሊቀመንበር እና የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፥ አፍሪካ በቴክኖሎጂ ልማት እያስመዘገበችው ያለውን ተስፋ ሰጪ እርምጃ የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለማቃለል ማዋል ይጠበቅባታል ብለዋል። 

ዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገራትና የፋይናንስ ሥርዓቱም አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለማቃለል እያከናወነችው ያለውን ስትራቴጂክ የልማት ሥራ መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። 

በፓን አፍሪካ እሳቤ ይፋ የሆነው አህጉራዊ የአረንጓዴ ኢንዱስትሪያላይዜሽን ኢኒሺዬቲቭም የታዳሽ ኃይል አማራጭ የልማት ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባው አፅንዖት ሰጥተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብለዋል። 

ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ አስተማማኝ ምላሽ ለመስጠት የሚወጡ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችን እና ሕግጋትን በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አፅንዖት ሰጥተዋል። 

በአፍሪካ ሕብረት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለአባል ሀገራቱ የአቅም ግንባታ ድጋፍ የሚያደርግ አህጉራዊ የአየር ንብረት ፋይናንስ ክፍል ተደራጅቶ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 

የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ድጋፍ የሚያደርጉ ለጋሽ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግን የገቡትን ቃል እየፈጸሙ እንዳልሆነ ነው የገለጹት። 

በመሆኑም አፍሪካ አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የፋይናንስ አቅሟን ማጎልበት እንደሚጠበቅባትም አስገንዝበዋል። 

በመድረኩ የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴን ጨምሮ የሀገራት የግብርና ዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top