"ሰላም የሁሉም መሰረት ስለሆነ ሰላማችንን መጠበቅ አለብን" ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

11 ቀን በፊት
"ሰላም የሁሉም መሰረት ስለሆነ ሰላማችንን መጠበቅ አለብን" ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወለጋ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር ሰላም የሁሉም መሰረት ስለሆነ ሰላማችንን መጠበቅ አለብን ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በከፈለው መስዋዕትነት በራሱ ቋንቋ የመጠቀም፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር እና ባህሉን የማሳደግ ነጻነት ማግኘቱን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዛሬ ይህን ድል አጽንተን ለቀጣይ ድል መነሳት እንጂ የተመለሱትን ጥያቄዎች እንደ አዲስ ማንሳት አይገባም ብለዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በነፍጥ የሚመለስ ጥያቄ ባለመኖሩ ጥያቄዎቻችን ሊመለሱ የሚችሉት በውይይት እና በመደማመጥ ብቻ መሆን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡  

የኦሮሞ ህዝብ የመደማመጥ እና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ወርቃማ ባህል እያለው አሁን እየተከሰተ ባለው የሰላም እጦት ምክያንት ያልተገባ መስዋዕትነት እየከፈለና ልማቱም እየተጓተተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይ ወለጋ ላይ ለረጅም ጊዜ በተከሰተው የሰላም አጦት ምክንያት ለሁሉም የሚተርፍ ሀብት ያለው አካባቢ ሳይለማ መቆየቱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ ይህን የሚያካክስ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

እየተጓዝን ያለነው ፈጣሪያችንን እና ህዝባችንን አስቀድመን ስለሆን ከብልፅግና ጉዟችን የሚገታን የለም ሲሉም ነው የገለፁት፡፡

ብልፅግናን ለማፋጠን እና ኢትዮጵያን በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል ማዳበር እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሚመጥናት ብልፅግና ላይ ለማድረስ የሀሳብ ልዩነቶችን በንግግር በመፍታት በወንደማማችነት መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዘን መነሳት አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top