የጳጉሜ ቀናት ስያሜዎችን ሰጥተን ስናከብር የነገ ትውልድን እያሰብን ነው-አቶ ከበደ ዴሲሳ

12 Days Ago 351
የጳጉሜ ቀናት ስያሜዎችን ሰጥተን ስናከብር የነገ ትውልድን እያሰብን ነው-አቶ ከበደ ዴሲሳ
የ2016 ዓ.ም አምስቱ የጳጉሜ ዕለታት ስያሜዎችን እና የአከባበር ሁኔታቸውን በተመለከተ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሰጥቷል፡፡
 
መግለጫውን የሰጡት የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ቀናቶቹ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ሕብረ ብሔራዊነት በሚገልጹበት መንገድ መጪውን ትውልድ ታሳቢ አድርገው እንደሚከበሩ ተናግረዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት በሕብረቷ እና በልጆቿ ጥረት ፈተናዎችን አልፋ እዚህ መድረሷን ያወሱት አቶ ከበደ፣ በዚህም የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችላለች ብለዋል፡፡
 
የኢትዮጵያውያን የጋራ አሻራ ውጤት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ ማድረስ፣ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሙሉ አምራችነት እንዲመጡ ማድረግ፣ የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ማደስ፣ አረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ታላላቅ ውጤታማ ፕሮጀክቶችን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል፡፡
 
ለግብርናው ዘርፍ በተሰጠው ልዩ ትኩረትም ከውጭ የሚመጣውን ስንዴ ማስቀረት መቻሉን እና በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርምም የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው ዕድገት እውን ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡
 
ሚኒስትር ዴኤታው በቀጣይ ዓመትም እነዚህን ስኬቶቻችንን አጠናክረን በመቀጠል የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ የሽግግር ወቅት የሆነችውን የጳጉሜ ዕለታትን በተለያዩ ስያሜዎች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን አመልክተዋል፡፡
 
ጰጉሜ አንድ "የመሻገር ቀን" ተብሎ መሰየሙን ገልጸው፣ ኢትዮጵያን ለማሻገር በተደረገው ጥረት የተገኙ ስኬቶችን እና በሂደቱ የገጠሙ ተግዳሮቶች የሚታሰቡበት ዕለት ነው ብለዋል፡፡
 
ጳጉሜ ሁለት "የሪፎርም ቀን" ተብሎ እንደተሰየመ እና ዕለቱም "ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት" በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር አስታውቀዋል፡፡
 
የኢትዮጵያን ተቋማት ለማዘመን፣ የአገልጋይነት መንፈስን በማጉላት የሕዝብን እርካታ መጨመር፣ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማስመዝገብ የኢኮኖሚ ስብራቶቻችንን ለመጠገን በሚያሳስብ መንፈስ እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
 
በስድሰት ዓመታት የተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎች በርካታ ለውጦችን ማምጣታቸውን የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ በሌላ በኩል የአገልግሎት መዝረክረኮችን እና እርካታ ማጣትን ሪፎርሙ በቀጣይነት የሚሠራባቸው ነው ብለዋል፡፡
 
ባለፉት ሦስት ዓመታት እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ በዚህ ዓመት መጨረሻ እርምጃዎች መወሰድ መጀመራቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይ ዓመትም ይህንን አጠናክሮ በመቀጠል የኑሮ ውድነቱን በተሻለ ሁኔታ ለመቅረፍ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
 
"ሕብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው ጳጉሜ ሦስት ባለፉት ስድስት ዓመታት ሉዓላዊነታችን ላይ የተጋረጡ ፈተናዎች የሚታሰቡበት ዕለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
 
እነዚህ ፈተናዎችም በአመራር ብቃት ቢታለፉም ይህ ብቻ በቂ እንዳልሆነ እና ሙሉ ልዓላዊነታችንን ለማስከበር በቀጣይ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አስፈላጊነት ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡
 
ከቀኑ ስድስት ሰዐት ላይ ሁሉም ሕዝብ የሚሳተፍበት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል እና የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የመዘመር ክንውን እንደሚኖርም አስታውቀዋል፡፡
 
"ሕብራችን ለሰላማችን" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው "የሕብር ቀን" ተብሎ የተሰየመው ጳጉሜ 4 መሆኑን አቶ ከበደ ገልጸዋል፡፡
 
ሕብር በቋንቋ፣ በባህል፣ በእምነት፣ በመልክአ ምድር እና በሕዝቦች መስተጋብር የሚገለጽ መሆኑን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ሕብራዊ ማንነቶች ጎልተው የሚታዩባት ሀገር ነች ብለዋል፡፡
 
በዚህ ሕብራዊ ማንነታችንም ፈተናዎችን አልፈን እዚህ እንደደረስን ሁሉ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረን መቀጠል በሚያስችለን መልኩ ይከበራል ብለዋል፡፡ ጧት ከ12 ሰዓት ጀምሮ ሰዎች በጋራ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ሁሉ የጋራ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንደሚደርጉ ተናግረዋል፡፡
 
"የነገ ቀን" ተብሎ የተሰየመው ጳጉሜ አምስት ቀን "የዛሬ ትጋት ለነገ ትሩፋት" በሚል እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡ ዕለቱ የነገውን ትውልድ ታሳቢ አድርገው እየተሠሩ ያሉ የሀገር ግንባታ ሥራዎች የሚታሰቡበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
 
ባለፉት ስድስት ዓመታት ታቅደው የተሠሩ ሥራዎች የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ አዲስ አበባን የማደስ፣ በሳይንስ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች፣ የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት፣ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ እንቅስቃሴዎች ለዚህ አብነት ናቸው ብለዋል፡፡
 
ቀናቱን ስንከብር የነገውን ትውልድ ታሳቢ ባደረገ እና ለቀጣይ እርምጃዎቻችን ስንቅ በሚሆንበት መልኩ መሆን እንዳለበት ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያሳሰቡት፡፡
 
ለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top