“የኢትዮጵያን ህልውና የሚበይኑት የተፈጥሮ ሀብቶች…”

14 Days Ago 727
“የኢትዮጵያን ህልውና የሚበይኑት የተፈጥሮ ሀብቶች…”
  1. ማደሪያ ያገኘው ባይ

ከዓለማችን ረዥሙ ወንዞች አንዱ የሆነው የዓባይ ወንዝ ጥቁር ዓባይ እና ነጭ ዓባይ ተብሎ ሁለት መነሻዎች አሉት። ከግሽ ዓባይ ተነስቶ በጣና አቋርጦ የጢስ ዓባይ ፏፏቴን ቀስተ ደመና ፈጥሮ ወደ ካርቱም በማቅናት ከወንድሙ ነጭ ዓባይ ጋር ካርቱም ላይ የሚገናኘው የእኛው ዓባይ ከኢትዮጵያ ህልውና ጋር የተሳሰረ እና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ ከኢትዮጵያ ደጋማ ክፍል የሚመነጭ ወንዝ የኢትዮጵያን ህልውና ከሚበይኑት የተፈጥሮ ሀብቶቿ መካከል ዋነኛው ነው።

ኢትዮጵያ የዓባይን ከ85 በመቶ የምታበረክት ሀገር ነች፡፡ ከቪክቶሪያ ሀይቅ ከሚመነጨው ነጭ ዓባይ ጋር ካርቱም ላይ ከተቀላቀለ በኋላ ግብፅን አጠጥቶ የኢትዮጵያን አፈርም ለገብጽ በገጸ በረከት አቅርቦ ወደ ሜድትራኒያን ባህር ይገባል።

ዓባይ ዓመቱን ሙሉ ፍሰቱ ከሌሎች ወንዞች የሚለይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ተራራማ አካባቢዎች የሚኖረው ዝናብ በወንዙ ፍሰት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ጥቁር ዓባይ እና ነጭ ዓባይ ሕብር ፈጥረው በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ለሚገኙ ሀገራት ሕዝቦች የሥልጣኔ መሰረት ሆነው ኖረዋል፡፡

ዓባይ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች እንዲስፋፉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። ከኢትዮጵያ ደጋማ ክፍሎች አጥቦ የሚወስደው ለም አፈር ለግብፃውያን እና ለሱዳናውያን የግብርና እና ሥልጣኔ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ ኖሯል።

ሱዳን እና ግብፅ በተለይ ደግሞ ግብፅ የዓባይን ውሃ እና የኢትዮጵያን ለም አፈር በመጠቀም ለዕድገታቸው ሲጠቀሙበት ቢኖሩም፣ በአንጻሩ የወንዙን 85 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ባይተዋር ሆና ኖራለች፡፡ ለዘመናት በተደረገባት ጫና የደጇን ውሃ መጠቀም ያልቻለችው ኢትዮጵያ ዓባይን በእንጉርጉሮ እና ሥነ-ቃል ስታሞግሰው ኖራለች፡፡ ዓባይ የሚያሳድረው አጥቶ በደጃቸው እያለፈ እንደሆነ የታዘቡት ኢትዮጵያውያን በቁጭት "ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል" እያሉ  ሲተርቱ ኖረዋል፡፡

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ግን የኢትዮጵያውያንን የዘመናት ቁጭት ወደ ተስፋ የቀየረ ብሥራት ተሰማ፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዓባይ ማደሪያ ሊሆን፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ ብርሃን ሊሆን ጅማሮው ተበሰረ። ግድቡ በአፍሪካ ካሉት የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በትልቅነቱ ግንባር ቀደሙ ነው። የግድቡ ዓላማ ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ነው። የኢትዮጵያውያን የይቻላል መንፈስን የሚያነቃ የዚህ ትውልድ ሀውልት ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡፡

ኢትዮጵያ ይህን ግድብ ለመሥራት ስትነሳ “ትልቁን የውሃ ድርሻ የማበረክተው እኔ ስለሆንኩ እንዳሻኝ የመጠቀም መብት አለኝ” በማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ የናይል ተፋሰስ ሀገራት በጋራ ተወያይተው ሁሉንም በሚጠቅም መልኩ በወንዙ እንዲጠቀሙ በማለም “የናይል ተፋሰስ ሀገራት ኢኒሼቲቭ” እንዲቋቋም በማድረግ ነው፡፡ ስምምነቱ አንዱ የተፋሰሱ ሀገር ሊሠራ ያሰበውን ፕሮጀክት አዋጭነት እና በተፋሰሱ ሀገራት ላይ ሊያደርሰው የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በጋራ ውይይት መስመር እንዲይዝ የሚያግዝ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ውሃውን በብቸኝነት ሲጠቀሙ የኖሩት ግብፅ እና ሱዳን የግድቡን መሠራት በበጎ አልተመለከቱትም። በተለይም ግብፅ የቅኝ ግዛት ውሎችን በመጥቀስ የውሃ ድርሻዬ የምትለው እንዳይነካ አንዳንዴ በማስፈራራት ከስምምነቱ ውጭ ለመሆን እየሞከረች ነው፡፡

የኢትዮጵያውያን የዘመናት ህልም የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዛሬ እነ ግብፅ እንዳሉት ውሃም ሳያስጠማቸው ለኢትዮጵያ ብርሃን መስጠት ጀምሯል፡፡ አራት ተርባይኖች ኃይል ማመንጭት ጀምረዋል፡፡ እስከ መጪው ታኅሳስ ድረስ ሰባት ተርባይኖች ሥራ እንደሚጀምሩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

  1. ከኢትዮጵያ ውጭ የማያምርበት ቀይ ባሕር

የአፍሪካ ቀንድን ከህንድ ውቅያኖስ ጋር የሚያገናኘው ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ባሕር ነው። ኢትዮጵያ ከቅርብ ዘመናት ወዲህ በተሠራባት ደባ ከባሕሩ የሚገባትን ድርሻዋን እንዳታገኝ ተደርጎ ቢቆይም በቀይ ባህር ወሳኝ የታሪኳ አካል ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም ከአክሱም ዘመነ መንግሥት እስከ ኢሕአዴግ ዘመን ድረስ ቀይ ባሕር ወሳኝ የንግድ መስመሯ እንደነበር ታሪክ ምስክር ነው። ከጥንት ታላላቅ ሥልጣኔዎች አንዱ የሆነው የአክሱማውያን መንግሥት በስትራቴጂያዊ መንገድ በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ከፍተኛ ንግድ ሲያካሄድ የነበረ ሲሆን፣ እንደ አዱሊስ ያሉ የቀይ ባሕር ወደቦችን ይቆጣጠርም ነበር። ይህም አክሱማውያን ከሮም፣ ከሕንድ፣ ከዓረቢያ እና ከሌሎች የአፍሪካ ጋር የነበረውን ንግድ የሚያሳልጥበት ነበር። እንደ ወርቅ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዕጣን እና ቅመማ ቅመም ያሉ እቃዎችን ወደ ውጭ ለመላክ እና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለማስገባት ይጠቀሙበት ነበር።

  1. የቀይ ባሕር ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ

የቀይ ባሕር ክልል በዘመናዊ ዓለም ጂኦ-ፖለቲካ ውስጥ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያለው ባሕር ነው። ይህ መስመር ለሸቀጦች እና ለነዳጅ መጓጓዣ ዋነኛ የንግድ መስመር በመሆኑ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ኮሪደር መረጋጋት እና ደህንነት ላይ ጠንካራ ፍላጎት አላት። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንደ ጅቡቲ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ካሉ ቀይ ባሕርን ከሚያዋስኑ ሀገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር፣ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ወደ ዓለም አቀፍ ንግድ መስመር የሚወስዳትን አስተማማኝ የባሕር በር ማግኝት ላይ ያተኩራል።

ኤርትራ በ1985 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ተገንጥላ ነጻ መንግሥት ከሆነች በኋላ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ የሆነች ሲሆን፣ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ዘንድ ስለ ባሕር በር እንዳይነሳ መንገዱ ሁሉ ተዘግቶ ቆይቷል፡፡ ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ህልውና አካል በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቀይ ባሕር መግቢያ መስመር ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ባብ-ኤል-ማንዴብ ዳርቻ በሚገኘው የጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ ሆና ትገኛለች። 95 በመቶ የሚሆነውን ምርት ከውጭ የምታስገባው እና ወደ ውጭ የምትልከው በዚሁ ወደብ ሲሆን፣ ለአገልግሎቱ የምትጠየቀው ክፍያ እና ቢሮክራሲው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም። በየጊዜው እየናረ የመጣው እና በውጭ ምንዛሬ በሚከፈለው የወደብ ኪራይ ወደ ሀገር ወስጥ በሚገቡት ሸቀጦች ላይ የሚጣለውን ዋጋ እያናረው ቀጥሏል፡፡ የቀይ ባሕር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑም ነው ኢትዮጵያ ከአካባቢው ሀገራት ጋር ጠንካራ ትስስር ለማስቀጠል እና በቀጠናው የፀጥታ እንቅስቃሴዎች ላይ በትኩረት የምትሠራው።

ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የቀይ ባሕርን መስመር ማግኘት ቅንጦት ሳይሆን የህልውናዋ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ቡና፣ ጨርቃ ጨርቅ እና እንስሳት የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ በነጻነት የምትጠቀምበት መውጫ በር ማግኘት ወሳኝ ነው። የቀይ ባህር ቅርበት ኢትዮጵያ ወደ ህንድ ውቅያኖስ በመግባት፣ ከእስያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር ለመገናኘት እና የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ያስችላታል።

የዚህ አካባቢ ሰላም መናጋት አጠቃላይ የንግድ እንስቃሴ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ኮሪደር ላይ የሚፈጠረው የሰላም መደፍረስ ለራሷ ህልውናም ለአካባቢውም አለመረጋጋት አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ በዚህ ረገድም ያላትን ሚናም ከፍ ማድረግ ትፈልጋለች፡፡ በሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች እና እንደ ምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) በመሳሰሉ ቀጣናዊ ድርጅቶች በንቃት መሳተፏ ለቀይ ባሕር ቀጣና ደህንነት እና መረጋጋት ያላትን ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ነው።

ኢትዮጵያ በቀጥታ ወደ ቀይ ባሕር ሊያስገባት የሚችለውን ወደብ የማግኘት መብቷን ጠይቃለች፡፡ ይህን ታሪካዊ መብቷን የጠየቀችው ግን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፍለጎት የማንንም ጥቅም መጻረር ሳይሆን የጋራ ተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን ማረጋገጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም ከኤርትራ ጋር ግንኙነቷን መልሳ ከመሰረተች በኋላ እንደ ምፅዋ እና አሳብ ያሉ ስትራቴጂያዊ ወደቦችን በስምምነት ለመጠቀም ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ የቀረው የኢትዮጵያን በቀጠናው ጎልታ መውጣት በሚያሳስባቸው ወገኖች አደናቃፊነት ነው።

  1. መውጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተገነባው በገንዘብ እና በላብ ብቻ ሳይሆን በደምም ጭምር ነው፡፡ እሳቸው እንዳሉት ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ሥራውን ለማደናቀፍ ከ15 ሺህ በላይ የታጠቁ ኃይሎች በአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ ለግድቡ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከቦታው ለማድረስ በአማካይ እስከ 45 ቀናት ድረስ ይፈጅ እንደነበር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በዚህ ሂደት በመንገድ ላይ የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማምከን የፀጥታ አካላት የከፈሉት ዋጋ ውድ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህም ነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን ላብ እና ደም የተገነባ የትውልድ ማኅተም ነው የተባለው፡፡

ሌላው ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ የሆነው ቀይ ባሕር ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ኢሕአዴግ ዘመን ድረስ ቀይ ባሕርን ሳትጠቀም የኖረችው ለጥቂት ጊዜያት ነው፡፡ በነዚህ ጊዜያት ሁሉ ግን ኢትዮጵያ የባሕር በሯ እንዲዘጋባት ያልተሠራ አሻጥር አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያን ቅኝ መግዛት ያልቻሉት ምዕራባውያን በእጅ አዙር ሲያደርጉአቸው በነበሩአቸው ተፅዕኖዎች እና በውስጥ ባለው አለመግባባት ምክንያት በሂደት ከባሕር በር እየተገለለች መጥታ ዛሬ ወደብ አልባ ሆናለች፡፡ "ኢትዮጵያ የባሕር በር ባይኖራትም ገንዘቧን ከፍላ ትጠቀማለች፤ አሰብም ቢሆን የግመሎች መሰማሪያ ከመሆን ያለፈ ጥቅም አይሰጥም" የሚል አስተዋይነት የጎደለው አቋም መያዛቸው እነሆ ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ ዛሬ ትውልዱ ከቀይ ባሕር የሚገባውን ድርሻ የሚጠይቅበት ጊዜ ደርሷል፡፡ የዛሬ የኢትዮጵያ ፍትሃዊ ጥያቄ ካልተመለሰ እየጨመረ ያለው የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ ዕድገት እየገፋ ሄዶ በራሱ ጊዜ አካባቢውን ማጥለቅለቁ አይቀርም፡፡ በዚያ መንገድ የሚመጠው መፍትሔ ደግሞ አካባቢው ላይ ቀውስ ከመፍጠር ያለፈ አይሆንም፡፡ ምዕራባውያን ብዙ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘው ባሕር ተሻግረው የሰፈሩበት ቀይ ባሕር ላይ ኢትዮጵያ ድርሻ አይኖራትም ማለት ፍትሃዊ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ቀጣዩ ትውልድ ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ የቀይ ባሕር ባለቤትነቱን መመለሱ አይቀርም የሚባለው፡፡

የኢትዮጵያ በዓባይ እና ቀይ ባሕር ላይ የሚገባትን መጠየቅ እንደ ግብፅ እንቅልፍ የሚነሳው ሀገር የለም፡፡ ለዘመናት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ስትሠራ የኖረችው ግብፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ኢትዮጵያን ለሚበጠብጡ ነጭ ለባሾች መደበኛ በጀት ይዛ የማተራመስ ሙከራዋን ቀጥላለች፡፡ ሱዳንን ጋልባ ኢትዮጵያን ለመውጋት ስትፎክር ከርማ ሙከራዋ ሳይሳካ ሱዳንን “አኬልዳማ” አድርጋ ወጥታለች፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ሶማሊያን ላይ ተፈናጥጣ ኢትዮጵያን ለማተራመስ የጀመረችው እንቅስቃሴ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህን ሁሉ ፉከራ እና ዙረት ያመጣው የኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ስምምነት መፈራረም ነው፡፡ ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን የሰውን ድንበር አልፋ አትገፋም ሲመጡባት ግን እንዴት እንደምትመልስ ታውቃለች፤ ግብፅም ይህን ስለምታውቅ ነው በውስጥ ጉዳያችን እና በአካባቢው ባሉት ክፍተቶች ሁሉ እየተጠቀመች የሌባ ሥራ የምትሠራው፡፡

ቀጠናው እንዳይረጋጋ የሚፈልጉ ሀገራት ኢትዮጵያ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ለዘመናት የሚችሉትን አድርገዋል፡፡ ለረጅም ጊዜ በተሠራባት አሻጥር የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ፈርሶ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነች በኋላ የሌሎችን እጅ መጠበቅ ግዴታ ሆኖባታል፡፡ የቀጠናው ሰላምም ባሕሩ ላይ እንደልብ በሚፈነጩ ወንበዴዎች እና አሸባሪዎች ምክንያት እየታወከ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ባይፈርስ ኖሮ ዛሬ በቀይ ባሕር ላይ የተፈጠረው ቀውስ የመፈጠር ዕድል ጠባብ እንደነበር የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዓባይ እና ቀይ ባሕር ህልውናችንን የሚበይኑ፣ የመጥፋታችንም የመልማታችንም ምክንያት የሚሆኑ ናቸው ያሉት፡፡ አዎ ኢትዮጵያ እየጠየቀች ያለው የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ፍትሃዊ ጥያቄ ከተመለሰ ሁለቱም ለሁሉም የሚበቁ ሲሆን፣ እንደ ከዚህ በፊቱ ኢትዮጵያን መግፋት ከቀጠለ ግን ቀጠናው ወደማያበራ ቀውስ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአካባቢው ሀገራት የቤት ቀጋ የውጭ አልጋ ከመሆን ትብብርን አስቀድመው እምቅ ሀብቱን መጠቀም ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ጥያቄም ፍላጎትም ይኸው ነው፡፡ ለዚህም ነው "ቀይ ባሕር እና ዓባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ ናቸው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top