የሉዓላዊነት ዘንጎች ከጦርነት እስከ ዲፕሎማሲ

8 Days Ago 337
የሉዓላዊነት ዘንጎች ከጦርነት እስከ ዲፕሎማሲ

ሉዓላዊነት ምንድን ነው? ሉዓላዊነት ማለት ያለ ምንም ውጫዊ ጣልቃ ገብነት ራስን ለማስተዳደር የሚያስችል የአንድ ሀገር የሥልጣን የበላይነት ነው። በዓለም አቀፍ መርህ መሰረትም ነጻነት እና የራስ አገዛዝ የሚያረጋግጥ የሀገራት መብት ነው።

የተሟላ ሉዓላዊነት የከፍተኛ ሥልጣን ባለቤትነት፣ የግዛት አንድነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነት፣ የህግ የበላይነት፣ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት እና የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሉዓላዊነት

የኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ነጻነቷን ጠብቃ በመቆየት እና የውጭ ወራሪዎችን አሳፍራ በመመለስ ትታወቃለች፡፡ ይህ ደግሞ ለረዥም ጊዜ በአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ቀንበር ስር ሲማቅቁ ለነበሩት የአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ቀንዲል እንደትሆን አድርጓታል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ ነጻነት ብቻ ይበቃል ብላ ሳትቀመጥ ለአፍሪካ ነጻነትም ዋጋ ከፍላለች።

የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ታሪክ ጥንታዊ ነው። በአክሱማዊ ዘመነ መንግሥት የነበራት ሥልጣኔ ከአካባቢው አልፎ በዓለም አቀፍ ንግድ እና ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ሚና ተጫውታለች። የአክሱም ተፅእኖ ቀይ ባህርን ተሻግሮ ወደ ዓረቢያ ልሳነ ምድርና ከዚያም ወደ አውሮፓ እና ሩቅ ምሥራቅ የተሻገረ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በየትኛውም ዘመን ሊተናኮሏት የመጡትን የውጭ ኃይሎች የታገሰችበት ወቅት አልነበረም፡፡ በሀገር ውስጥ እንኳን ሽኩቻ ቢኖር በልጆቿ ክንድ ወራሪዎችን ስትከላከል ኖራለች፡፡ የግብፅ ኃይሎችን ተደጋጋሚ ትንኮሳ መክተው ወራሪዎቹን የበረሃ ሲሳይ ያደረጉት አፋሮች፣ ከመሃዲስት ጋር ሲፋለሙ የተሰውት አጼ ዮሐንስ፣ ዶጋሊ ላይ የጣሊያንን ወራሪ ከአፈር የደባለቁት እነ ራስ አሉላ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ቀንዲሎች ነበሩ፡፡

ባህር ተሻግሮ የመጣውን የጣሊያን ወራሪ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ መሪነት በአድዋ ድል ያደረገችው ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ ቀጥላለች፡፡ የአድዋ ድል አፍሪካን እንዳሻቸው ሲገዙ ለኖሩት የአውሮፓ ኃይሎች የሽንፈት በርን የከፈተ፣ በነሱ ቅኝ ግዛት ሲሰቃዩ ለኖሩት አፍሪካውያን ደግሞ የነጻነት ሻማ የለኮሰ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በሙሶሎኒ እብሪት በፋሽስት ኢጣሊያ ለአምስት ዓመታት የተወረረች ቢሆንም ሉዓላዊነትን ግን ሙሉ በሙሉ አሳልፋ አልሰጠችም። ጀግኖቹ የኢትዮጵያ አርበኞች በጎበዝ አለቆች እየተመሩ ጣሊያንን መቆሚያ መቀመጫ ሲያሳጡት ነበር አምስት ዓመታቱ ያለፉት፡፡ በዓለም አደባባይ ባሰማችው ትንቢት መሳይ አቤቱታዋ የፋሽስቱን እኩይ ድርጊት ከማጋለጧም በላይ የመንግሥታቱን ማኅበር ገመና አደባባይ ላይ አስጥታለች፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያ ላይ ሲሳለቁ የነበሩት አውሮፓውያን ለራሳቸው እሳት ውስጥ ሲገቡ ኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን አውጃለች፡፡

የመንግሥታቱ ማኅበር መሥራች እና አባል መሆኗ የሉዓላዊነቷ እና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ሚናዋን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የአፍሪካ ሕብረት መሥራችነቷ ደግሞ ለአፍሪካ ነጻነት እና ሕብረት ያላትን ፍላጎት ማሳያ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪዎችን አሳፍራ በመመለስ ነጻነቷን አስከብራ የኖረች ብትሆንም በውስጥ የሚነሱ ግጭቶች ግን ፈተናዎቿ ናቸው፡፡ እነዚህ ውስጣዊ ግጭቶች አብዛኛውን የውጭ እጆች ያሉበት ቢሆንም፣ ችግሮችን በንግግር ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ የመፍታት መሞከር ልማዳችን ውጤቶችን ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ምንም ያክል ውስጣዊ ግጭቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጫናም ሆነ በውስጣዊ ፍላጎት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በሰላም ለምፍታት ጥረት እያደረገ ይገኛል። በሰላማዊ መንገድ የማይመለሱት ላይም ተመጣጣኝ እርምጃዎችን እየወሰደ የሀገርን ሉዓላዊነት ማክበሩን ቀጥሏል፡፡

ኢትዮጵያ ዛሬም ትላንት በጀግኖቿ ክንድ አስጠብቃ የኖረችውን ሉዓላዊነቷን የሚያስቀጥሉ ልጆች እናት ነች፡፡ ለዘመናት ያልተኙላት ታሪካዊ ጠላቶቿ ዛሬም በሀገር ውስጥ ባሉ ቅጥረኞቿ አማካኝነት ሰላም ሊነሷት እንቅልፍ ቢያጡም ልጆቿ ህልማቸውን ቅዠት የሚያደርጉ ልጆቿ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡

የተሟላ ሉዓላዊነት

ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት ወራሪዎቿን መክታ የኖረች ብትሆንም ሉዓላዊነቷን እንዳይሟላ የሚያደርጉ ችግሮችን ስትጋፈጥ ኖራለች፡፡ ከነዚህም ዋነኛው የምግብ ዋስትናን አለማረጋገጧ ነው፡፡ እነ አክሱምን፣ ላሊበላን እና ጎንደርን የሠራን እጅ ለልመና ከመዘርጋት በላይ ውርደት የለም፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም የታደለችውን ኢትዮጵያን አቅም አሟጥጦ ካለመጠቀም የመጣ ነው፡፡ የበሰለ የምታበቅል ሀገር ይዘን የተቀቀለ ስንዴን ከለመንን፣ ለም አፈር እና በቂ ውሃ ይዘን ከግብፅ ብርቱካን እያስመጣን፣ በቀንድ ከብቶች ብዛት እየታወቅን ወተት ከውጭ እያስገባን፣ የሚሠሩ እጆችን ይዘን የሰውን እጅ እያየን የተሟላ ሉዓላዊነት አለን ማለት አንችልም፡፡

ለዚህም ነው ባለፉት ስድስት ዓመታት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጎ ተሠርቶ ውጤት እየመጣ ያለው፡፡ በግብርና ላይ በተደረገው ሪፎርም በዓመት ከአንድ በላይ ማምረት ተችሏል፤ ስንዴ ስትለምን የነበረችው ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ መግዛትን አቁማ ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች፡፡ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ትሩፋት በሆነው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ትልቅ እምርታ እያሳየች ትገኛለች፡፡ በኢትዮጵያውያን ላብ እና ደም የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የተሟላ የሚሆነው እነዚህ የተጀመሩት ተግባራት ተጠናክረው ሲቀጥሉ እና የተሻለ ውጤት ሲያመጡ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀገሩን የሚወድድ እና ለመጪው ትውልድ የሚያስብ ዜጋ ሁሉ ይረባረባል፡፡ መጪው ትውልድ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነች እና ለእርዳታ እጇን የማትዘረጋ ሀገር መረከብ አለበት፡፡

ይህ በታሪክ ውስጥ የነበረ የሉዓላዊነት መከበር እና ማስከበር ዳር ድንበርን እና ወራሪ ሃይልን አሳፍሮ በመመለስ ላይ ውድ ህይወትን እየሰጡ በደም የጸናች ሀገር ለማቆየት ተችሏል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ፈልጋ የጀመረችው ጦርነት ባይኖርም ሊደፍሯት የሞከሩትን ሁሉ አሳፍራ ክብሯን አስጠብቃ እየኖረች ያለች ሀገር ነች። ይህ ደግሞ አሁን ላላው ትውልድ የመጽኛ እና ዳግማዊ ዓድዋን ለመተግበር የሚያስችል የታሪክ እርሾ እና ወረት ሆኖ ያገለግላል።

አሁን ደግሞ በዚህኛው ዘመን ሌላኛው የሉዓላዊነት ማስከበሪያው መንገድ ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ እየሆነ መጥቷል። በእርግጥ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲውም መስክ ሉዓላዊነቷን አስከብራ ለሌች መከበርም ተግታ የሰራች እና ውጤትም ያመጣች መሆኗ አያጠያይቅም። እናም ይህ የዲፕሎማሲ ሥራ ዛሬም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስከበሪያ ሆኖ የትውልዱ አንገት ቀና ማድረጊያ ተግባር ሆኗል።

ሉዓላዊነታችንን በጥረታችን እናረጋግጣለን!

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top