አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ እጅግ አነስተኛ ድርሻ ቢኖራትም በአየር ንብረት ለውጥ ግን ገፈት ቀማሽ ሆና ቆይታለች።
አህጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለው ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ከዋንኛ የበካይ ጋዝ ለቃቂና ከበለፀጉ ሀገራት የፋይናንስ ድጋፍ እንድታገኝ ጥረቶች ከተጀመሩ ቆይቷል።
ባለፉት 5 ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 40 ቢሊየን ችግኝ በመትከል ታሪክ የሰራችው ኢትዮጵያ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የመሪነት ድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች።
ለዚህም ነው በመስከረም ወር የሚካሄደው እና ከ2500 በላይ ልዑካን የሚሳተፉበት የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማስተናገድ የተመረጠችው።
ለአየር ንብረት ለውጥ ፈጣን ዓለም አቀፍ መፍትሄ እንስጥ፣ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአፍሪካ አረንጓዴ ልማትን እውን ለማድረግ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ድጋፍ ማፈላለግ የጉባኤው መሪ ቃል ነው።
2ኛው አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7.5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ይፋ በተደረገበት በአዲስ አበባ ዓለም አቀፉ የኮንቬንሽን ማዕከል የሚካሄድ ይሆናል።
ከመላው አፍሪካና ከዓለም የተውጣጡ ከ2500 በላይ ባለድርሻ አካላት ለ3 ቀናት በሚሳተፉበት ጉባኤ 100 እንግዶች ንግግርና ገለፃ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
የአፍሪካ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤውን በተመለከት ለባለድርሻ አካለት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ የአፍሪካ ህብረት
እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ ድረገፅ ትላንት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።