የማንኮራፋት ችግር እንቅልፍ ማሳጣት ብቻ አለመሆኑን ያውቃሉ?

2 Days Ago 313
የማንኮራፋት ችግር እንቅልፍ ማሳጣት ብቻ አለመሆኑን ያውቃሉ?

ማንኮራፋት በእንቅልፍ ወቅት በአፍ እና በአፍንጫ ውስጥ ያለው የአየር ፍሰት በከፊል ሲዘጋ ይከሰታል።

ይህም በጉሮሮ ውስጥ ያሉ ህብረ ሕዋሳት እንዲርገበገቡ እና ከፍተኛ ድምፅ እንዲፈጠር ያደርጋል።

የአንገት በላይ ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ኃይለማርያም ታፈሰ፥ ማንኮራፋት በአጠገባችን በሚተኛ ሰው ላይ አዕምሮአዊ እንዲሁም አካላዊ ጉዳት እንደሚያስከትል  በኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ  97.1 ላይ በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

የማንኮራፋት ችግር የሚከሰተው በላይኛው የመተንፈሻ አካላችን መጥበብ ምክንያት ሲሆን፤ በዚህ ጠባብ መስመር ውስጥ አየር በሚተላለፍበት ጊዜ የላንቃችንን ክፍል በማርገብገብ የሚከሰት ድምፅ መሆኑን ዶክተር ኃይለማርያም ገልጸዋል።

ለማኮራፋት በምክንያትነት ከሚነሱ ጉዳዮቸ መካከል በአደጋ ምክንያት አፍንጫ አከባቢ ሲጎዳ፣ እንዲሁም በአፍንጫችን ውስጥ የሚገኙት ስጋዎች አብጠው ጠባብ የአየር ማስተላለፊያዎች የሚኖሩ ከሆነ፤ በሌላ በኩል እጢ እና መሰል ነገር በአፍንጫችን አካባቢ ከተከሰተ ለማንኮራፋት መንስኤ ሊሆን እንደሚችሉ የሕክምና ባለሙያው አብራርተዋል። 

አነስተኛ እና ብዙ ጉዳት የሌላቸውን የማንኮራፋት አይነቶች እቤት ውስት በቀላሉ ልንከላከላቸው እንድምንችላቸውም አንስተዋል። 

ማንኮራፋት ካስቸገረን የአልጋችንን ትራስ ከፍ ማድረግ እንዲሁም በጀርባችን ከመተኛት ይልቅ በጎን በመተኛት፤ የተሻለ የአየር ዝውውር እንዲኖር ማድረግ እንደሚቻል ባለሙያው ይመክራሉ። 

አብዛኛው የማንኮራፋት አይነት ብዙ ችግር የሚያስከትል ባይሆንም፤ በተለየ ሁኔታ ግን ወደ ሕክምና ሄደው መታየት የሚያስፈልጋቸው የማንኮራፋት አይነቶች እንደሚኖሩም አንስተዋል።

ሰዎች በሚተኙበት ሰዓት የማንኮራፋቱ ድምፅ ከፍተኛ ሲሆን፤ በእንቅልፍ ሰዓት ዕንቅልፍ የመቆራረጥ፣ ትንፋሽ የመቆራረጥ፣ በእንቅልፍ ልብ በጣም መጨነቅ እና መገለባበጥ የሚከሰተ ከሆነ ሕክምና ማግኘት አስፈላጊ እንደሆነ አንስተዋል።

በተለየ ሁኔታ ደግሞ እድሜያቸው ከ3 እስከ 6 ዓመት የሚገኙ ህጻናት ከባድ ማንኮራፋት ከታየባቸው ወደ ህክምና ቦታ ሄደው መታየት ይኖርባቸዋልም ነው ያሉት።

በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህፃናት አፍንጫቸው ጀርባ የሚያድግ በተለምዶ የአፍንጫ ቶንሲል የሚባል በሽታ እንዲሁም ቶንሲል በተደጋጋሚ ስለሚገጥማቸው፤ ከባድ ማንኮራፋት ሊገጥማቸው እንደሚችል እና አንዳንድ ጊዜም በትንታ መልክ ከእንቅልፋቸው ሊቀሰቅሳቸአው እንደሚችል ነው ባሙያው የገለፁት።

ይህን መሰል ምልክቶችን ወላጆች ካስተዋሉ ህፃናትን ወደ ሕክምና ተቋማት ወስዶ ማሳየት እንደሚገባ ነው ዶክተር ሐይለማርያም ታፈሰ የተናገሩት።

ይህን መሰል የማንኮራፋት ችግር ያለባቸው ህፃናት አስፈላጊውን ህክምና የማያደርጉ ከሆነ ለከፍተኛ ጉዳት ሊጋለጡ እንደሚችሉም  ተናግረዋል። 

ማንኮራፋት በከፍተኛ ደረጃ የመተንፈስ ስረዓቱን ካስተጓጎለው፤ በቂ የሆነ የኦክስጂን ዝውውር ስለማይኖር የተለያዩ ተጓዳኝ ህመሞችን ሊያስከትል ስለሚችል በወቅቱ ወደሕክምና ተቋማት በመሄድ አስፈላጊውን ሕክምና ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያው ይመክራሉ።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top