በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የጎፍር መከላከል ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር አደን አብዶ ተናገሩ። ኃላፊው ይህን ያሉት በኢቲቪ አዲስ ቀን የዜና መሰናዶ በነበራቸው ቆይታ ነው።
ኃላፊው ካሳላፍነው አመት ጀምሮ በአዋሽ ተፋሰስ ላይ የጎፍር መከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው አስታውቀዋል።
በዋና ዋና ተፋሰሶች ላይም የጎርፍ አደጋው የበዛ ስለመሆኑም ነው ኢንጂነር አደን አብዶ ያነሱት።
በአዋሽ ተፋሰስ አከባቢዎች ላይ ዝናብ በመጣ ቁጥር ጎርፍ ስጋት እንደሚሆን ያነሱት ኃላፊው፤ የመልከዓምድሩ አቀማመጥ ለዚህ አደጋ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝም ገልፀዋል።
የአዋሽ ወንዝ ውኃ ፍሰት መያዝ ከሚችለው በላይ በሚጨምርበት ወቅት አቅራቢያው ባሉ ማህበረሰብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስም ገልጸው፤ በዚህ አከባቢ ላይ በየዓመቱ ሥራ እንደሚፈልግም ተናግረዋል።
በውኃ እና ኢነርጂ ሚንስቴር የተቀናጀ የውኃ ሀብት አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ደበበ ደፈርሶ በበኩላቸው፤ ክረምት በመጣ ቁጥር ጎርፍ ስጋት እንደሆነ አንስተዋል።
በሀገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ከመሬት አቀማመጥ እና ከዝናብ መጠን ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸው ከተሞች መኖራችውንም አቶ ደበበ ተናግራዋል።
ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ የሚመጣ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ለጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በሀገሪቱ የተከሰተ ከፍተኛ የዝናብ መጠን ያስከተላቸው ጉዳቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
በተለያዩ ጊዜያት የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ሥራዎች እንደሚሰሩ ያነሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፥ ሆኖም ግን የጎርፍ አደጋውን ለመከላከል ከፍተኛ ሥራ እና ገንዘብ እንደሚያስፈልም ተናግረዋል።