ኢትዮጵያ ሻምፒዮን የሆነችበት 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ

1 Day Ago 246
ኢትዮጵያ ሻምፒዮን የሆነችበት 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ

በአውሮፓውያኑ 2007 በአፍሪካ ሕብረት የተበሰረው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ የአህጉሪቱን የተራቆተ መልክዓ ምድር አረንጓዴ በማልበስ በሳህል ቀጠና የሚኖሩ ሚሊዮኖችን ህይወት የመለወጥ ዓላማ ያለው ፕሮጀክት ነው።

በፕላኔታችን ላይ ካሉት የሥነ-ህይወት ፕሮጀክቶች ሁሉ ትልቁ እንደሆነ የተነገረለት እና በአፍሪካ ውስጥ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ ዘላቂነት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስፈን ታልሞ የተጀመረ ነው።

ይህ ፕሮጀክት በ22 የአፍሪካ ሀገራት እየተተገበረ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያንቀሳቀሰ ነው።

ይህን ፕሮጀክት ለመደገፍ ከ14 ቢሊየን ዶላር በላይ መሰባሰቡም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረሃማነትን የመዋጋት ኮንቬንሽን (United Nations Convention to Combat Desertification) ገጽ ላይ ተመላክቷል።

በዚህም በአውሮፓውያኑ 2030 በአሁኑ ወቅት ወደ በረሃማነት የተለወጠውን 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ አረንጓዴነት በመመለስ 250 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ማመንጨት እና 10 ሚሊዮን አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችን መፍጠርን ዓላማው አድርጓል፡፡

ስለተፈጥሮ እና ስለምድራችን ፈተናዎች የሚዘግበው ሞንጋቤይ (Mongabay) የተባለ ድረገጽ ባወጣው መረጃ በረሃማነትን ለማስቆም የሚደረገውን ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች የዘገየ ቢሆንም ተስፋ የሚጣልበት ውጤት እያሳየ ነው፡፡

ድረ-ገጹ ያናገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን ዛፍ የመትከል ብቻ ሳይሆን አካባቢውን የሚለውጥ እንዲሁም የገቢ ምንጭ እንደሆነ አድርጎ እንዲመለከተው ግንዛቤ በመፍጠር ሁለንተናዊ ተሳትፎን እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡

በዚህ መንገድ ተሞክሮም በማሊ፣ ቡርክናፋሶ፣ ኒጀር፣ ጋና እና በሌሎች ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ውጤታማ እንደሆነ ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ስኬቶች እና ቀጣይ ጉዞ

ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ አደገኛነት የተረዳችው ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጀምራለች፡፡

የአረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በመጠበቅ ምርት እና ምርታማነትን የሚያጎለብት እንዲሁም እድገቷን እና ብልፅግናዋን ለመጪዎቹ ትውልድ የሚያስቀጥል ነው፡፡

አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግናን እውን የምታደርግበት ተግባርም ነው። የኢትዮጵያ ልምላሜ ብቻውን በቂ ስላልሆነም አረንጓዴ አሻራን በጎረቤት ሀገራት እና በመላው አፍሪካ እንዲስፋፋም ብርቱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከተተከሉት 40 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ 90 በመቶው መጽደቃቸው ተገልጿል፡፡

እንደ ግብርና ሚኒስቴር መረጃ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የለም አፈር መከላትን ከ1.9 ቢሊየን ወደ 208 ሚሊየን ቶን ዝቅ እንዲል አስችሏል፡፡

በዚህ ዓመት "በመትከል ማንሰራራት" መሪ ቃል 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መርሐ-ግብር ወጥቶ ሥራ ተጀምሯል፡፡

በዘንድሮው መርሐ ግብር ግብርናን ታሳቢ ያደረጉ እና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለመትከል ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራም ይገኛል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ኮንቬንሽን መስፈርት መሰረትም በ2011 ዓ.ም 17.2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን፣ ባለፉት ዓመታት በተሠራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ወደ 23.6 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡

ኢትዮጵያ ደኗን ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ወደ ነበረው 40 በመቶ ለመመለስ ስትራቴጂ ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡ በ2030 አሁን ያለውን ከ23.6 በመቶ በላይ የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ ነው፡፡

ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጎን ለጎን የደን ምንጣሮን የመቀነስ ሥራም ስለተሠራ ዓመታዊ የደን ውድመት ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺህ ሄክታር ቀንሷል፡፡ አዳዲስ ችግኞችን መትከል እና የደን ጭፍጨፋን መቀነስ መቻሉ የደን ሽፋን እንዲሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ እና አፕል ያሉ ተክሎች የምሥራች ፌሬያቸውን ሰጥተው ለምግብነት ደርሰዋል፡፡

ይህ መርሐ ግብር ኢትዮጵያውያን በየጓሮአቸው ችግኞችን ተክለው የሚንከባከቡበትን ባህል የፈጠረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም በውጤቷ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝታበታለች፡፡

በዚህ ዓመትም 7.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ኢትዮጵያ እንደተለመደው ሁሉ ስራዋን ጀምራለች።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top