በሰሜን ቪየትናም የሚኖሩ ነዋሪዎች አትክልት ከጓሯቸው፣ ከበረታቸው ከብት እንዲሁም አሳ ከኩሬያቸው አይጠፋም።
ቪየትናሞች የአትክልት ስፍራን፣ የከብት እርባታን እና የአሳ ገንዳዎችን በአንድነት አጣምሮ የያዘ ባሕላዊ የግብርና ዘዴያቸውን (VAC) ይሉታል፤ ምህጻረ ቃሉ ከቋንቋቸው የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ጓሮ /ኩሬ/የከብቶች ማቆያ ሥፍራ ማለት ነው።
በ1960ዎቹ ቬየትናምን በመሩት በፕሬዚደንት ሆቺ ሚኒህ እቅድ ወጥቶለት በስራ ላይ መዋል ቢጀምርም የታሰበውን ያህል ሳይተገበር ቆይቶ ነበር፡፡
በ1981 እያንዳንዱ ቤተሰብ በምግብ ራሱን ከመቻል አልፎ ለሌላው እንዲተርፍ ሲባል ፖሊሲ ተቀርፆለት በተለይ በተራራማ አካባቢ በሚኖሩ የሰሜን ቪየትናም ነዋሪዎች ዘንድ መተግበር የጀመረ የግብርና ዘዴ ነው።
በ'ቫክ' የግብርና ሥርዓት መሰረት አንድ ሰው ባለው የጓሮ ቦታ ላይ አትክልትና ፍራፍሬን ያመርታል፤ በአትክልቶቹ ተረፈ ምርት እንስሳቱንና አሳዎቹን ይመግባል፤ የእንስሳቱ ፍግ ለአትክልቶቹ እንደማዳበሪያነት ያገለግላል እንዲሁም አሳዎቹ የሚመገቡት አልጌ እንዲያድግ ይረዳል።
በዚህ መሰረት የተጀመረው የሥስትዮሽ የተቀናጀ ግብርና አሁን ላይ ከ85 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ በሰሜን ቪየትናም የሚኖሩ ሰዎች የአትክልት ማሳ እና የእንስሳት እርባታ በአንድ ላይ አላቸው፡፡ ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሆኑት ቬትናማውያን ደግሞ የግል የአሳ እርባታ ያላቸው ናቸው።
ይህ ቬትናማውያን በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ በሚል የተጀመረ የተቀናጀ ግብርና ዘዴ ዛሬ ላይ አድጎ ጥቂት የማይባሉ ቬትናማውያን ኑሯቸውን ሙሉ በሙሉ በዚህ ላይ ብቻ መስርተው እስከመምራት ደርሰዋል።
በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ በምግብ ራሳቸውን ከመቻልም አልፎ ገቢያቸውንም ማሻሻል መቻላቸውን የፋኦ መረጃ ያመለክታል።
ማንኛውም ሰው በግቢው ውስጥ ባለው ጓሮ ይህንን የተቀናጀ የግብርና ዘዴ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን የሚችልበት በመሆኑ በሁሉም ዘንድ ባሕል ሊሆን እንደሚገባ ይነሳል፡፡