"የባሕር በር ካለህ ዓለም ሁሉ ገበያህ ነው"

1 Day Ago 120
"የባሕር በር ካለህ ዓለም ሁሉ ገበያህ ነው"
የኢኮኖሚ ጫና ያለባቸው ሀገራት የባሕር በር አማራጭ ከሌላቸው በልማት ማነቆዎች የተጠፈነጉ እንደሚሆኑ የምጣኔ ሀብት እና የሕዝብ ፖሊሲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ኮሊየር ይገልፃሉ።
 
"የባሕር በር ካለ ዓለም ሁሉ ገበያህ ነው፤ ከሌለ ግን ከጥቂቶች ጋር ብቻ ትገበያያለህ" በማለት ሃሳባቸውን ያስቀምጣሉ። ይህንኑ ሃሳብም በርካቶች ይስማሙበታል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "በቀይ ባሕር ዙሪያ ያሉ የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነት እናከብራለን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ሆና እንድትቀጥል የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት እነርሱም ሊያምኑ እና ሊያከብሩ ይገባል" ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
 
በታሪክ ብሎም በሕግ የባሕር በር አማራጭ የማግኘት መብት ያላት ኢትዮጵያ፣ ቀይ ባሕርን የማስተዳደር ተሳታፊነት ላይ ልትካተት ይገባል የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪ አበራ ሃኢብሳ ናቸው።
 
ተመራማሪው ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ያለው መረጋጋት እና ሰላም ዘላቂ እንዲሆን በማድረግ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ የባሕር በር አማራጭ እንድታገኝ መስራት አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
 
ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላትን ሀገር ቆልፎ ማቆየት አግባብ እንዳልሆነ በመግለፅ፤ ይህንንም ለማስቀረት የትውልዱን ጥያቄ ማስመለስ ይገባል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
 
የፖለቲካ ተመራማሪው አስራት ኤርሜሎ በበኩላቸው፤ በኢኮኖሚ ለመጠንከር ማምረት ብቻ ሳይሆን የተመረተውን ወደ ወጪ የገበያ ንግድ የሚቀርብበት አማራጭ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
 
ኢትዮጵያ ቡና እና ሌሎችም በአምራችነት የምትታወቅባቸውን ግብዓቶቿን በበርካታ የዶላር መጠን እንደምትልክ ገልፀው፤ ይህም የእያንዳንዳችንን ኪስ የሚነካ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
 
አክለውም ሉዓላዊነትን በማጎልበት በባሕር በር ጉዳይ መነጋገርና እና ተጠቃሚነትን ማሳደግ አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው ብለዋል፡፡
 
በአፎሚያ ክበበው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top