እየሩሳሌም ካሳ ከጊዜ በኋላ የአካል ጉዳት ቢገጥማትም ይህን ተቋቁማ በኬተሪንግ ስራ ከራሷ አልፋ ለሌች የስራ ዕድል መፍጠር የቻለች ጠንካራ ሴት ናት።
እየሩሳሌም ዛሬ በዚህ ስራ ተሰማርታ ሕይወቷን ከመቀየሯ በፊት፣ በዓረብ ሀገር ስራ ላይ በነበረችበት ወቅት በአጋጣሚ መንገድ ላይ በደረሰባት የመኪና አደጋ ለአካል ጉዳት መዳረጓን ትናገራለች።
በአደጋው የጀርባ አጥንት ጉዳት ያጋጠማት ወጣቷ፣ ምንም እንኳን አስፈላጊው ሕክምና ለ7 ወራት ያህል ቢደረግላትም መራመድ እንዳልቻለች ትገልፃለች።
ታዲያ ነገሩን ይበልጥ ከባድ ያደረገው እየሩሳሌም ከደረሰባት አደጋ በኋላ ወላጅ እናቷ ስለአደጋ ሲሰሙ በድንጋጤ ሕይወታቸው ማለፉ ነበር።
እየሩሳሌም የሰው ሀገር ሆና እናቷ ሕይወታቸው ማለፍን ስትሰማ ድንገት የገጠማት የአካል ጉዳት እና ኀዘን እጅጉን ከባድ የሆነ የመንፈስ ስብራት እና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከቷት እንደነበር ትናገራለች።
ወደ ሀገሯ ከመጣችም በኋላም በኀዘን ብዛት ብዙ ዓመታትን በተስፋ መቁረጥ ማሳለፏን አንስታለች።
"መኖር ስላለብኝ እንጂ ያ ሁሉ አልፎ ዛሬ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አላሰብኩም" ያለችው ወጣቷ፤ ሕይወት በዚያ መንገድ እንደማይቀጥል እና ያለፈን መመለስ እንደማይቻል በመረዳት አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ወስና ትነሳለች።
ዛሬ ላይ ታዲያ ሁሉንም ነገር ተቋቁማ ኑሮን ለማሸነፍ ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚሆኑ ምግቦችን በማዘጋጀት ገቢ ከማግኘት ባሻገር ለሌሎችም የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለች ሲሆን ያቋረጠችውን ትምህርትም ቀጥላለች።
በትንሽ ካፒታል ሥራ የጀመረችው እየሩሳሌም፣ ወደፊት ነገሮች ቢመቻቹላት ከዚህ በላይ ትልቅ ሕልም እንዳላትም ትገልጻለች።
እየሩሳሌም የአካል ጉዳት ያለበት ሰው መስራት እንደሚችል እና በጥንካሬ ሰርቶ ማሳያት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፋለች።