ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን ያመጣው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ

1 Day Ago 168
ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን ያመጣው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ
የሀገሪቱን ጥቅምና ሉዓላዊነት የሚያስከብር ዲፕሎማሲን በማስጠበቅ የዜጎች ጥቅምና እኩልነት ላይ የተመሰረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መተግበር ኢትዮጵያ የምትከተለው መርሕ ነው።
ይህ መርሕ ከዚህ ባለፈ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የመሰረተ ልማት ትስስርን እና ገፅታ ግንባታን በማጠናከር የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ አተኩሮ ይሰራል።
የውጭ ዲፕሎማሲ መርሑ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ለማስፋፋት፣ የቱሪዝም ፍሰትን ለመጨመር እንዲሁም እውቀትና ቴክኖሎጂን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው። ሰላምን በማስጠበቅ መልካም የሆነ የፖለቲካ ዲፕሎማሲን ለማጠናከርም ያስችላል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በቀጣናው ካላት ተሰሚነት ባሻገር፣ ቁልፍ ከሚባሉ ሀገራት ጥሩ የሆነ ዲፕሎማሲ መፍጠሯን የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ይናገራሉ።
ሀገሪቱ ባላት የዲፕሎማሲ ግንኙነትም በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያም ትልቅ ሥራ ተሰርቷል ብለዋል።
በብሪክስም ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ጥሩ ሥራዎችን በመስራት ላይ ትገኛለች ሲሉም አክለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶች መካሄዳቸውን አንስተው፤ ይህም የዲፕሎማሲው ስኬት ማሳያ ነው ብለዋል።
የታሪክና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ በቀጣናው የፈጠረችው በጋራ የመልማት ዲፕሎማሲ በሌሎች ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት እንድታገኝ መሰረት መጣሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የተረጋጋ ሰላምን የሚፈልግ ነው የሚሉት ዶ/ር አለማየሁ፤ በጋራ መልማት እንዲሁም በጋራ መጠቀም ላይ ያተኮረ ስለመሆኑም ነው የገለጹት።
ቀጣናው ትልቅ ጂኦፖለቲካ የሚካሄድበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በንግድና በልዩ ልዩ ትስስሮች አብረዋት መስራት ከሚፈልጉ ሁሉ ጋር ትሰራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የንግድ ትስስርን በመፍጠር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማጠናከር መቻሏንም አያይዘው አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በምትከተለው ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ የጋራ ልማትን ማጠናከር ከማስቻሏ ባለፈ፣ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በማሳደግ ጥሩ የሚባል ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውጤት ማግኘቷን ምሁራኑ ተናግረዋል።
በሐይማኖት ከበደ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top