የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኒው ዮርክ ከሚገኘው አዴልፊ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በረሃማነትን ለመከላከል ፕሮጀክት ቀርጾ እየሠራ ይገኛል፡፡
ይህ የተመድ በረሃማነትን የመከላከል ኮንቬንሽን (UNCCD) "መሬት ለሰላም ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ምድርን ማዳን" የሚል ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
ይህ ፕሮጀክት የመሬት ሥነ ምህዳራዊ ሕዳሴ በዓለም አቀፍ የሰላም እና የፀጥታ አጀንዳዎች ውስጥ እንዲካተት የሚሠራ ነው።
የመሬት ጥበቃ ስልቶችን በፀጥታ ፖሊሲዎች፣ በሰላም ግንባታ መርሐ ግብሮች እና ሌሎች ሰፋ ባሉ የልማት ማዕቀፎች ውስጥ መካተት እንዳለባቸው የዚህ ፕሮጀክት ሀሳብ ነው።
መሬት መልሶ እንዲያገግም ለማድረግ የሚፈስሰው መዋዕለ ንዋይ የመሬት መራቆትን ችግር ብቻ በመፍታት የሚወሰን ሳይሆን ይበልጥ ሰላማዊ እና አስተማማኝ የሆነ ዓለም ለመገንባት የማይተካ ሚና ይኖረዋል።
በዚህም ምክንያት ነው "መሬት ለሰላም" የሚለው አባባል የምድራችን ጤንነት ከማኅበረሰብ መረጋጋት ጋር የማይነጣጠል መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ተጠቅሷል።
መሬት መልሶ እንዲያገግም ማድረግ የግጭት መከላከል እና ሰላም ግንባታ መሰረታዊ ምሰሶ መሆኑን በመገንዘብ በዓለም አቀፍ የሰላም እና የፀጥታ አጀንዳ ላይ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተመድ ያሳስባል።
በተለይ በጣም በተጎዱ እና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ለመሬት ማገገም የሚሆን ተጨማሪ እና የተሻለ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ለጉዳዩ የተመደበው ፋይናንስ ዝቅተኛ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ለመሆኑ የምድር ማገገም እንዴት ለዓለም ሰላም አስተዋጽኦ ያደርጋል?
መሬት ለሚኖርባት ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምግብ፣ ውኃ እና መተዳደሪያ ምንጭ በመሆን ለሕይወታቸው፣ ለደኅንነታቸው እና ለክብራቸው ወሳኝ ነች።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ20 እስከ 40 በመቶ መሬት፣ እንዲሁም 60 በመቶ የሚሆነው አጠቃላይ ሥነ-ምህዳር በመጎዳቱ ግን ለዓለም ማኅበረሰብ ህልውና አስፈላጊ የሆነው የህልውና ምንጭ እየጠፋ እንደሆነ ጥናቱ ያመላክታል።
መሬት እየተበላሸ እና ፍሬያማነቱ እየቀነሰ መሄድ ደግሞ ለመኖር የሚያስፈልገውን ሀብት ፍለጋ በሚደረገው ፉክክርና አለመግባባትን እያባባሰ መጥቷል።
እነዚህ አለመግባባቶች በዓለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጎልተው ለሚታዩት ግጭቶች በተለይ በሀገራት መካከል ለሚፈጠሩት አለመግባባቶች ምክንያት በመሆን ላይ ናቸው።
ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 40 በመቶ የሚሆኑት የሀገር ውስጥም ሆነ አካባቢያዊ ግጭቶች መሬትን ጨምሮ ከተፈጥሮ ሀብቶች ጋር የተያያዙ እንደሆነም ነው የተመድ ሪፖርት የሚያሳየው።
ተመድ በሪፖርቱ የመሬት መራቆት ወደ ግጭትና ስጋት የሚያመራባቸውን አምስት ዋና ዋና መንገዶችን አድርጓል፡፡
የመጀመሪያው በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጥገኛ የሆነው የሰው ልጅ መተዳደሪያ፣ ሥራ እና ኢኮኖሚያዊ እድል እየቀነሰ መምጣት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለአደጋ የሚያጋልጥ ከመሆኑም በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ድርጊቶች ላይ እንዲሳተፍ በማነሳሳት ለግጭቶች መንስኤ መሆኑ ነው።
በመሬት መራቆት እና ምርታማነት እየቀነሰ መምጣት ምክንያት የሰብል ምርት መቀነስ፣ የምግብ ዋጋ መናር እንዲሁም የምግብ እና የውኃ እጥረት እንዲባባስ በማድረግ ማኅበራዊ አለመረጋጋት እና ግጭት ሊያስከትል መቻሉ ሌላኛው ምክንያት ነው።
ሦስተኛው ምክንያት ደግሞ የመሬት መራቆት ፍልሰት እና መፈናቀል እንዲጨምር በማድረግ ፍለሰቱ ከሚካሄድበት አካባቢ ማኅበረሰብ እና ፍልሰተኞች መካከል ውጥረት እና ግጭት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑ ነው።
የመሬት መራቆት የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ኪሣራ በየዓመቱ 6.3 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተገምቷል፡፡ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ፈተና ውስጥ በማስገባት መረጋጋት እንዳይፈጠር በማድረግ ግጭቶችን እያባባሰው ይገኛል።
አምስተኛው ምክንያት ከላይ የተጠቀሱ ግጭቶች ራሳቸው ለዘላቂ የመሬት አስተዳደር የሚያስፈልጉ ሥራዎች እንዳይሠሩ በማድረግ ወደ አጠቃላይ ቀውስ የሚያመራ መሆኑ ነው።
መሬትን ወደ ቦታዋ መመለስ እንደ ሰላም መፍጠሪያ ስትራቴጂ
መሬትን ወደ ቦታዋ መመለስ የአየር ንብረት ቀውስን በመፍታት ረገድ ያለው ሚና በተመለከተ ግንዛቤው እየጨመረ ቢመጣም፣ ዓለም አቀፍ ሰላም እና ትብብርን የማስፈን አቅሙ በአብዛኛው ችላ በመባሉ ነው ተመድ ይህን ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ያለው።
ጠንካራ እና ተግባራዊ የመሬት መታደስ የተቀናጀ የተፈጥሮ ጥበቃን ተግባራዊ በማድረግ የተፈጥሮ ሃብት አያያዝን ለግጭት መከላከል እና ለጋራ መፍትሔ መንገድ ይከፍታል።
እንደ ታላቁ አረንጓዴ ግንብ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክቶችም የጋራ አጀንዳ እና የትብብር መድረክን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
ይህም መተማመንን በመገንባት እና የጋራ የተፈጥሮ ሀብቶችን በተመለከተ በውይይት የጋራ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያስችላል። ጎሬቤት ሀገራትን ጭምር ታሳቢ ያደረገው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለዚህ ሌላኛው ማሳያ ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች የአካባቢን የመቋቋም አቅም በመጨመር የምግብ ዋስትናን እና ከማሻሻላቸውም በላይ የሀብት ምንጭ በመሆን በአካባቢዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመቀነስ የተረጋጋ ማኅበረሰብን ለመፍጠር ይጠቅማሉ።
መሬት መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ዘላቂ የመሬት አስተዳደር ከአየር ንብረት እና ሥነ-ሕይወታዊ ሀብት ጥበቃ ግቦች ጋር የሚሰናሰል በመሆኑ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን ለማሳካት ወሳኝ ነው።
የጋራ የመሬት ሀብቶችን ለማስተዳደር የጋራ እና ድንበር ተሻጋሪ ማዕቀፎችን ማመቻቸት ወሳኝ በመሆኑ የጋራ ሳይንሳዊ እና ቴክኒካዊ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማስቀመጥ ወደ ሥራ መግባት ወሳኝ መሆኑን ነው የተመድ ምክረ ሀሳብ የሚያሳየው።
የተገለሉ ማኅበረሰቦችን ጨምሮ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በማረጋገጥ የውሳኔ ሂደቱ አካል ማድረግ ደግሞ ለውጤታማነቱ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ይሆናል።
የመልሶ ማቋቋም ፕሮጀክቱ ውጤታማ የሚሆነው አሉታዊ ተፅዕኖዎችን በመለየት እና የመፍትሔ ሀሳቦችን በማስቀመጥ መተማመን ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ሲደረግ ሲሆን፣ በሥራው ላይ ለሚሳተፉት ደግሞ የጋራ አጀንዳን ማስፈጸም የሚያስችል የአቅም ግንባታ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ነው።
የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ መስጠት አንድም የመሬቱ ባለቤት ምድርን መልሶ በማደሱ ሂደት በመሬቱ ላይ ቋሚ ሀብት እንዲፈጥር የሚያስችል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የባለቤትነት ጥያቄ የግጭት መንስኤ እንዳይሆን በማድረግ ለግቡ መሳካት የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡
ኢትዮጵያ እና ውጤታማ የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራሟ
ኢትዮጵያ በመሬት እና አካባቢ ጥበቃ ረገድ ጉልህ እና ትልቅ እርምጃ ወስዳለች። በተለይም ባለፉት ስድስት ዓመታት በተገበረችው አረንደጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እያመጣችው ያለው ለውጥ ተጨባጭ እየሆነ መጥቷል።
ይህ ጥረቷ የተራቆቱ አካባቢዎችን አረንጓዴ በማልበስ የደን ሽፋንን በማሻሻል የሥነ-ምህዳርን ቀጣይነት እንድታረጋግጥ እያደረጋት ይገኛል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ባከናወነችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ40 ቢሊዮን ችግኞች በላይ ተክላለች፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ችግኞችን በዘመቻ ከመትከል ያለፈ ውጤት እያመጣ ይገኛል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ማኅበረሰቡ በየአካባቢው ያለውን መሬት የመጠበቅ ባህሉን እንዲያሳድግ፣ በየቀዬው ሀገር በቀል ዛፎችን እንዲተክል እና ዛፎችን ወደ ሀብት እንዲቀይር እያደረገው ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ 22 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልበስ አቅዳ እስከ ፈንጆቹ 2023 ድረስ 15 ሚሊዮን ሄክታር መሬት አረንጓዴ ማልበሷን በጥናት ያረጋገጡት የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ሆርቲካልቸር፣ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ቀለሙ ደሴ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካባቢ ጥበቃ ድርጅት ጭምር ምስክርነት የሰጠው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለበርካቶች መሬት እንድታገግም ከማድረግ ባለፈ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠራ፣ ቀጣናዊ ትስስርን እያሻሻለ እንዲሁም የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ እያሻሻለ ነው፡፡
ከተመድ የአካባቢ ጥበቃ ፖሊሲ ጋር የሚሄደው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ ለአርሶ አደሮች የይዞታ ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመስጠት አርሶ አደሮች ከደንነት ያለፈ የምግብነት ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን እንዲተክሉ እያስቸለ እንደሆነም ተመድን ጨምሮ በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ባለድርሻዎች ምስክርነታቸወን ሰጥተዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናውን ያረጋገጠ እና የተረጋጋ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በአርአያነት እየመራችው ነው፡፡
በለሚ ታደሰ