ዓለም አቀፍ የኔልሰን ማንዴላ ቀን በየዓመቱ ሐምሌ 11 ቀን ይከበራል።
ዕለቱ የሚከበረው ደቡብ አፍሪካዊው የፀረ-አፓርታይድ ታጋይ፣ የፖለቲካ መሪ እና በጎ አድራጊ የሆኑትን የኔልሰን ሮሊህላህላ ማንዴላን የልደት ቀን ምክንያት በማድረግ ነው።
የዘንድሮ የማንዴላ ቀን የሚከበረው "ድህነትን እና ኢ-ፍትሃዊነትን ለመዋጋት አሁንም ዕድሉ በእጃችን ነው" በሚል ሃሳብ እንደሚከበር ኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን ያወጣው መርሐ ግብር ያመላክታል፡፡
ዕለቱ የሚከበረው የኔልሰን ማንዴላን ስኬቶች በማሰብ ብቻ ሳይሆን ግለሰቦች በማኅበረሰባቸው ላይ በጎ ተፅዕኖ እንዲያመጡ እና ፍትሃዊ እና ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ ዓለም አቀፍ የተግባር ጥሪ ለማቅረብ ነው።
ዋናው መልዕክቱ ኔልሰን ማንዴላ ለ67 ዓመታት ለማኅበራዊ ፍትህ ሲታገሉ ኖረዋል እና ይህን ታሳቢ አድርጎ ሰዎችም ሰላማዊ ዓለምን ለመገንባት አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ለማነሳሳት ነው።
ይህም ሰዎች ኔልሰን ማንዴላ በሕይወት ከኖሩባቸው 67 ዓመታት አንዳንድ ደቂቃ በመውሰድ የ67 ደቂቃዎች በጎ ፈቃደኝነት፣ ለማኅበረሰብ አገልግሎት እና ለደግነት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የሚያበረታታ ነው።
የዚህ ዓመት መሪ ሃሳብ ማንዴላ ማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን ለመዋጋት እና በፍትሕ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ማኅበረሰብ ለመገንባት የእድሜ ልክ ቁርጠኝነት ከማሳየታቸው ጋር በጥብቅ ይገናኛል።
ኔልሰን ማንዴላን እና ዓለም የሚያስታውሰውን የእርሳቸውን አስተዋፅኦ ለማክበር ቀን እንዲወሰን ሐሳብ የመነጨው እ.አ.አ በ2009 ነው።
የመጀመርያው መደበኛ ያልሆነ የማንዴላ ቀን የተከበረው በ2009 ከማንዴላ 91ኛ የልደት ቀን ጋር ሲሆን፤ የትምህርት፣ የኪነ ጥበብ፣ የገንዘብ ማሰባሰቢያ እና የበጎ ፈቃድ ዝግጅቶች ተከናውነዋል።
ኔልሰን ማንዴላ ለሰላም እና ነጻነት ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ በመገንዘብም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ሐምሌ 11 ቀን በይፋ "የኔልሰን ማንዴላ ዓለም አቀፍ ቀን" ሆኖ እንዲከበር ደንግጓል።
ተመድ ዕለቱ እንዲከበር ሲወስን ማንዴላ ሕይወታቸውን ሙሉ የሰው ልጆችን ለማገልገል መታገላቸውን በማሰብ የግጭት አፈታትን፣ የሰብዓዊ መብት ጥበቃን ፣ የፆታ እኩልነትን፣ የሕፃናት እና ሌሎች ተጋላጭ ቡድኖች መብቶችን ለማሻሻል በማሰብም ነው፡፡
ዕለቱ ድህነትን ለመዋጋት የሚደረገው ትግል እና ማኅበራዊ ፍትህ ለማስፈን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዴሞክራሲ ባህልን ለማጎልበት በሚሠራው ሥራ ላይ ግንዛቤ ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው።
ዕለቱ በተመድ ዕውቅና ካገኘ በኋላ የመጀመሪያው ኦፊሴላዊ የኔልሰን ማንዴላ ዓለም አቀፍ ቀን የተከበረው እ.አ.አ. በሐምሌ 18 ቀን 2010 ነበር።
የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ እ.አ.አ. በታኅሳስ 2015 የኔልሰን ማንዴላ ዓለም አቀፍ ቀን በልዩ ትኩረት እንዲከበር ድንጋጌውን አሻሽሏል፡፡
በማሻሻያው መሰረትም የእስር ቤት ሰብዓዊ ሁኔታዎችን ማሻሻል እና እስረኞች ታርመው የኅብረተሰብ ክፍል መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ማድረግ በአከባበሩ ላይ እንዲካተት ተወስኗል።
የእስር ቤት ሠራተኞች የሚያከናውኑትን ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆነ ማኅበራዊ አገልግሎት አድርጎ መመልከት እንደሚገባ የማሻሻያ ድንጋጌው ላይ ተካትቷል።
ይህ የውሳኔ ሃሳብም የተሻሻለውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእስረኞች አያያዝ ስታንዳርድ ደንብ ያፀደቀ ሲሆን፤ ለ27 ዓመታት በእስር ቤት ላሳለፉት ማንዴላ ክብር ሲባል ሕጉ "የኔልሰን ማንዴላ ሕግ" ተብሎ እንዲታወቅ ተደርጓል።
የኔልሰን ማንዴላ የፀና አቋም፣ ለዓላማ ፍርሃትን የማሸነፍ ፅናት እና ለፍትህ የመቆም የማይናወጥ እምነት ማሳያ ነው።
ኔልሰን ማንዴላ በአፓርታይድ ሥርዓት ላይ በነበራቸው ትግል ምክንያት ለ27 ዓመታት ፅኑ እስረኛ ነበሩ።
ይሁንና አፓርታይድን አሸንፈው ነፃ ከወጡ በኋላ ያንን ጊዜ ያስታወሱት በምሬት ሳይሆን የዘር ልዩነት ላይ ያልተመሰረተች ዴሞክራሲያዊት ደቡብ አፍሪካን በመፍጠር ነበር።
እ.አ.አ. በ1994 ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ሽግግርን በመምራት የሀገሪቱ የመጀመሪያው በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
የማንዴላ ፅናት አንድ ሰው በዓላማ ለፍትህ እና ለዕውነት ከታገለ ዓለምን በተሻለ ሁኔታ የመለወጥ ችሎታና ኃላፊነት መወጣት እንደሚችል ማሳያ ነው።
ማንዴላ የታገሉለት ዓላማ የሕዝብ አገልግሎት፣ ሰብዓዊ መብት እና ማኅበራዊ ፍትህ እሴቶችን የሚያስፋፋ መሆኑን በማሰብ ሁሉም ለተሻለ ዓለም እንዲሠራ ማነሻሻ ሆኖ እያገለገለ ነው።
ሕይወታቸው እና ተግባራቸው ብዝኃነትን ለማፅናት ምክክር፣ መግባባትን እና ዕርቅን የሚያበረታታ ሲሆን፣ ከድህነት እና ከኢ-ፍትሃዊነት ጋር ለሚደረገው ትግል ብርታት እንደሚሆን ይገለጻል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች በአካባቢያቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በመሥራት፣ አካባቢያቸውን በማጽዳት፣ ችግኞችን በመትከል፣ አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን በመርዳት፤ በአጠቃላይ በጎ ሥራዎችን በመሥራት ለማኅበረሰባቸው ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ ሐምሌ 11 ቀንን ያከብራሉ።
በለሚ ታደሰ