እንደ ሀገር ሕዝባችንን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ በማፍራት ላይ ይገኛል፡- አቶ አደም ፋራህ

11 Days Ago 184
እንደ ሀገር ሕዝባችንን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ በማፍራት ላይ ይገኛል፡- አቶ አደም ፋራህ
ኢትዮጵያን የመሰለ ድንቅና እምቅ የመበልፀግ አቅም ያላት ሀገር ተችሮን ለእርዳታ እጃችንን የምንዘረጋበት ጊዜ ይበቃል ብለን፣ እንደ ሀገር ሕዝባችንን ከተረጂነት እሳቤና ተግባር ለማላቀቅ የጀመርነው ጉዞ ፍሬ በማፍራት ላይ ይገኛል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
 
ልመናን ተጠይፎ እጅን እና እግርን አስሮ ከሚይዝ የተረጂነት እሳቤ ነፃ የሆነ ማህበረሰባዊ ውቅር ገንብተን፣በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን አረጋግጠን፣ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ለመጎናፀፍ እንድንችል ዕቅድ ነድፈን ወደ ስራ ገብተናል ሲሉ አቶ አደም በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል።
 
ዓላማውን በተሟላ ደረጃ ለማሳካት በየደረጃው ካለው አስፈፃሚ እና ፈፃሚ አካል ጋር የጋራ መግባባት ፈጥረን፣ በሁሉም ክልሎች ከ10.6 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የተሳተፈበት "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ለሀገራዊ ሉዓላዊነትና ክብር" በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ መድረኮች በማካሄድ ከህብረተሰባችን ጋር የጋራ መግባባትን ፈጥረን፣ እንዲሁም ዐብይና የቴክኒክ ኮሚቴዎችን አዋቅረን ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል በመልዕክታቸው።
 
በዚህም መነሻነት ሕዝባችን በአርበኝነት ስሜት ልመና በቃኝ ብሎ እንዲነሳና ከተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ ነፃነትን መጎናፀፍ ይገባናል የሚል ቁጭት እንዲፈጠርበት ተደርጓል ነው ያሉት።
 
እንደሀገር ሊኖረን የሚገባውን የፖሊሲ ነፃነት እና ተፅዕኖ አልባ የሉዓላዊነት ህልውና መጎናፀፍ የምንችለው ክብራችንን ለሚሰፈርልን ስንዴ መስዋዕት አድርገን ካላቀረብን ብቻ እንደሆነና ከተረጂነት ለመላቀቅም ብቸኛው መፍትሄ ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ ሕዝባችን ተረድቶታል ሲሉ ገልጸዋል።
 
ይህንን መነሻ በማድረግም በግብርናው ዘርፍ በስንዴ፣በሩዝ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በምግቤን ከጓሮዬ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎችም የልማት መርሐ-ግብሮች የተገኙ ውጤቶችን በማስፋት ስር የሰደደ የልመና እና የተረጂነት እሳቤን ከማህበረሰባችን የሞራል መዝገበ ቃላት ውስጥ ለመፋቅ መንቀሳቀስ ይኖርብናል ብለዋል።
 
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንድንችል የመንግስት የልማት ፕሮግራሞችን አቀናጅተን ተግባራዊ በማድረግ፣ በአንዳንድ ክልሎች የተጀመሩ ለምሳሌነት በኦሮሚያ ክልል "ቡሳ ጎኖፋን" የመሰሉ የህብረተሰቡ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት፣ በችግር ጊዜ ለወገን የመድረስ ባሕልን የሚያሳድጉ እሳቤዎችን፣ ተቋማትንና ተግባራትን በማዳበር፣ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች በአግባቡ ለይቶ ድጋፉን በራስ አቅም ለማቅረብ የሚያስችል ስራ በመስራት እና በቂ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያዎችን በማከማቸት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሙሉነት ልንሸጋገር ይገባል ነው ያሉት።
 
አቶ አደም ፋራህ በመልዕክታቸው፤በደም የተከበረው ሉዓላዊነታችንን በላባችን በማፅናት ከተረጂነት በመላቀቅ በራሳችን የምንቆምበትን አውድ መፍጠር ትውልዳዊ ግዴታችን ነውና ለዓላማው ግብ መምታት ሁላችንም የሚጠበቅብን ኃላፊነት መወጣት ይኖርብናል ብለዋል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top