ሁለገቡ የሀገር ባለውለታ - ኢንጂነር ታደለ ብጡል

11 Days Ago 213
ሁለገቡ የሀገር ባለውለታ - ኢንጂነር ታደለ ብጡል

በሥነጥበብ፣ በታሪክ እና በቅርስ ጠባቂነት፣ በንግግር አዋቂነት፣ በድርሰት ሥራዎቻቸው፣ በላቀ የምህድስን በሙያቸው እንዲሁም በበጎ አድራጊነት ሥራቸው ይታወቃሉ፡፡

ታታሪነትና እና ሀገርን መውደድ በተግባር ያሳዩን ሁለገብ ባለሙያ፣ ሁሉም በየዘርፉ እና በየአቅሙ ለሀገሩ ምን ማበርከት እንዳለበት ሠርተው ያሳዩ ሊቅ ናቸው፡፡

መኖሪያ ቤታቸው የኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ሰዎችን በሚዘክሩ ታሪካዊ እና ዕድሜ ጠገብ ሥዕላት፣ ምስሎች እና ፎቶግራፎች፣ ቅርጻ ቅርጾች እንዲሁም የኢትዮጵያን ታሪክ እና ቅርስ በተመለከተ በጽሑፎች፣ በሰነድ፣ በምስል፣ በድምፅ እና በቪዲዮ ያሰባሰቧቸው መረጃዎችና ቅርሶች የተሞላ እንደሆነ የቅርብ ወዳጆቻቸው ይመሰክራሉ።

ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ያላቸው ክብር እና ተቆርቋሪነት እንዲሁም ለሕዝባቸው ያላቸው ፍቅር እና ወገናዊነት በጣም ጥልቅ ነው ይባልላቸዋል።

ኢንጂነር ታደለ ብጡል ክብረት ታህሳስ 21 ቀን 1919 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥካሴ (የአሁኑ ኮከበ ጽባህ) ት/ቤት ተከታትለዋል። የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በአሜሪካ ዩንቨርሲቲ ኦፍ ዊል ካስሰን እና ቺካጎ የተከታተሉ ሲሆን፣ በስዊድን ስቶክሆልም ደግሞ በስተረክቸራል ዲዛይን  በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

ወደ ውጭ ለትምህርት ከማቅናታቸው በፊት በመንግሥት ባንክ ለ8 ዓመታት ያገለገሉት ኢንጂነር ታደለ፣ ስዊድን ሀገር በጆንማትሰን ኩባንያ ተቀጥረው የቬኔግሬን የሪሰርች ማዕከል ግንባታ ላይ መሥራት ጀመሩ፡፡

በስዊድን ሀገር በወቅቱ ረጅም በነበረው ባለ 25 ፎቅ ሕንጻ ሥራ ተቆጣጣሪ በመሆን፣ ኢራን ውስጥ በተሠራ የባንክ የምድር ቤት ገንዘብ ማስቀመጫ፣ ፖላንድ የሚገኝ ትልቅ ሆቴል ስትራክቸራል ዲዛይን ሥራዎችን ሠርተዋል።

ስዊድን እያሉ የ1953 ዓ.ም የእነጀነራል መንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አምባሳደር ከነበሩት ወዳጃቸው አቶ ተፈሪ ሻረው እና ከቅርብ ጓደኛቸው ኢንጂነር አሰፋ ብርሃነ ሥላሴ ጋር ሆነው ደግፈውት ነበር፡፡ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራው ሲከሽፍም ሁሉም ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው ለስደት ተዳረጉ፡፡

ኢንጂነር ታደለ፣ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የግዮን ሆቴልን የመዋኛ ገንዳ የሠራው መሐንዲስ ጉስታቭለን ከሚሠራበት ሀዩስ ኮንሱልት ቢሮ ተቀጥረው ሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ የራሳቸውን የሪል ስቴት እና የግንባታ ድርጅት አቋቁመው ሥራ ጀመሩ፡፡ በዚህም አሮጌ ቤቶችን እየገዙ አድሰው በማከራየት ሥራ ተሰማሩ፡፡

በ1966 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ በመከሰቱ የሀገራቸውን ሕዝብ ለመርዳት ከስዊድን ሕዝብ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድኃኒት፣ የሆስፒታል አልጋ፣ የኤክስሬይ መሣሪያዎች ስላገኙ የትራንስፖርቱን ወጪ ከራሳቸው ገንዘብ በመክፈል ቁሳቁሶቹን አምጥተው ለእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽነር አስረክበዋል፡፡

በተለያየ ጊዜ እርዳታዎችን ከስዊድን ሀገር እያሰባሰቡ የበጎ አድራጎት አገልግሎት መስጠታቸው፡፡ የአቅመ ደካሞች መርጃ ድርጅት፣ የገበሬዎች ማኅበር እና ለዕድገት በህብረት ዘማች ተማሪዎች የድጋፎቻቸው ተቋዳሾች ናቸው፡፡ በአዲስ አበባም 300 ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ትምህርት ቤት በገንዘባቸው ሠርተው አስረክበዋል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የማታ ትምህርትን ያስጀመሩት እርሳቸው መሆናቸውም ይነገራል፡፡ በታዋቂው አርበኛ የተሰየመውን ደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤትንም ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ኢንጂነር ታደለ  ናቸው፡፡

የአክሱም ሐውልት እና ሌሎች የኢትዮጵያ ቅርሶች ብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ አባል በመሆንም የዜግነት ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል፡፡ የአክሱም ሀውልትን  ለማስመለስ ከሌሎች ጋር በመሆን ከአሥራ ሰባት ዓመታት በላይ ታግለዋል፡፡ ሀውልቱን ለማስመለስ እንደ አርበኛም ጣሊያኖችን በመከራከር፣ እንደ ባለ ሀብት በገንዘባቸው፣ እንደ ምሕንድስና ባለሙያነታቸው የሐውልቱን አመላለስ የምሕንድስና ጉዳዮች አጥንቶ እንዲተገበር በማድረግ ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም ለመጻፍ በቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ከሀውልቱ መመለስ ጋር ተያይዞ "ኢትዮጵያዊ ፅናት" የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም እና 640 ገጾች ያሉት መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡

ኢንጂነር ታደለ ብጡል የተለያዩ ባህላዊና ትውፊታዊ ቅርሶችን ከተለያዩ ክፍላተ ዓለማት በራሳቸው ወጪ በመግዛት በመሰብሰብም ይታወቃሉ፡፡ የሰበሰቧቸውን ቅርሶችም በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ልዩ ልዩ ሙዚየሞች በመለገስ ታሪካዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ኢንጂነር ታደለ በኢትዮጵያ ታሪክ ጉዳይ እረፍት የላቸውም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በአውሮፓና በአሜሪካ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ነጻነትና ጀግንነት አስረድተዋል፣ ኢግዚቢሽኖችን አሳይተዋል። በአሜሪካ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ግብዣ ተደርጎላቸው ስለ አክሱም ሀውልት አወሳሰድ እና በኋላም ወደ ሀገሩ እንዲመለስ የተደረገውን ትግል በተመለከተ ሰፊ ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።

አኒጂነር ታደለ የምህንድስና ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ የተዋጣላቸውም ደራሲ ናቸው፡፡ ከድርሰት ሥራዎቻቸውም መካከል ማራዠት 1 እና 2፣ ሦስትዮሽ የግጥም ስብስቦች፣ ውለታ ፣ ከበደ ሚካኤል ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ መጽሐፈ ውይይት ከከበደ ሚካአኤል መኩሪያ ጋር የሚሉት ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪም በአፄ ቴዎድሮስ፣ በልዑል ዓለማየሁ፣ በሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ዙሪያ ከጻፏቸው መጻሕፍት ሌላ የአማርኛ የምልክት ቋንቋ መዝገበ ቃላትን አዘጋጅተው አሳትመዋል፡፡ በአጠቃላይ ከአሥራ አምስት በላይ መጻሕፍትን እንዳዘጋጁ ታሪካቸው ያሳያል፡፡

ኢንጂነር ታደለ ብጡር ለሀገራቸው በሠሩአቸው ሥራዎች በርካታ ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል፡፡ ከነዚህ ሽልማቶች መካከልም የአክሱምን ሐውልት ለማስመለስ በነበራቸው ሚና፣ ከኢፌዴሪ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ(ዶ/ር) እጅ የወርቅ ሜዳሊያ፣ ከትግራይ ክልል መስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር የወርቅ ካባ፣ ከአክሱም ሕዝብ የአክሱም ሐውልቶች ቅርፅና ሐረግ ያለበት ከእንጨት የተሰራ ታጣፊ የፎቶግራፍ ማቀፊያ ተሸልመዋል፡፡

በበጎ አድራጎት ሥራዎቻቸው፣ በግል ገንዘባቸው እና ሌሎችን አስተባብረው ለሠሩአቸው ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ዕድገት ላደረጉት አስተዋጽኦ በርከታ ሽልማቶችን ተሸልመዋል፡፡ የ2008 ዓ.ም የዓመቱ በጎ ሰው ድርጅት ሽልማት በቅርስና ባህል ዘርፍ፣ ከንባብ ለሕይወት ድርጅት የዕድሜ ዘመን ታላቅ የጥበብ ባለውለታ ዋንጫ ከሽልማቶቻቸው መካከል ነው፡፡

ከ2002 እስከ 2009 ዓ.ም የዲካ ትራቨል ኤንድ ሎጅስ አስጎብኝ ድርጅት የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ በመሆን ለፈፀሟቸው ከፍተኛ ተግባራት ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡ እንዲሁም ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት እና ለኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማኅበር ላደረጉላቸው ልዩ ልዩ ድጋፎችም ዕውቅና አግኝተዋል፡፡ ከፊንላንድ ኤምባሲ ለምነው ባስገኙት 650 ሺህ ብር ባለ 2 ፎቅ ትምህርት ቤት በማሰራታቸውም ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እጅ የተማሪዎች መመረቂያ የሆነ ውብ ሥዕል ተሸልመዋል፡፡

የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትን እና የአዲስ አበባ ዲዛይን ትምህርት ቤት ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ከፍ እንዲል በኮሚቴ አባልነታቸው ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ስም በዲዛይን ትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በአርቲስት በቀለ መኮንን እጅ የተሠራ ውብ ሥዕል ተሸልመዋል፡፡

የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ማኀበር የሕፃናት ትምህርት ቤት እና የማኀበሩን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከፊንላንድ ኤምባሲ እና ከካናዳ ድርጅት ለምነው በአገኙት ገንዘብ ሙሉ እድሳት እንዲደረግ ላደረጉት አስተዋፅዖም ከማህበሩ ፕሬዚዳንትና ከፊንላንድ መስማት የተሳናቸው ማኀበር ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በተስፋዬ ባዩ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top