አቶ ጥላሁን ከበደ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በአንድ ጀምበር 100 ቤት የመገንባት መርኃ ግብርን አስጀመሩ

1 Mon Ago 178
አቶ ጥላሁን ከበደ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በአንድ ጀምበር 100 ቤት የመገንባት መርኃ ግብርን አስጀመሩ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በአንድ ጀምበር 100 ቤት የመገንባት መርኃ ግብርን አስጀምረዋል።
 
በአቶ ጥላሁን ከበደ የተመራ ልዑክ በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የቤት ግንባታ እና መታሰቢያ የሚሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
 
አቶ ጥላሁን ከበደ መርኃ ግብሩን ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለፁት፤ ትላንት የገጠሙንን ፈተናዎች ወደ ዕድል በመቀየር በተሻለ ጥንካሬ ነገን ልናስቀጥል ይገባል ብለዋል።
 
ሐምሌ 15 ለክልሉ ጥቁር ቀን ነበር ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች የፍቅር ጥግን በማሳየት ታሪክ ሰርተው ማለፋቸውን ጠቅሰዋል።
 
እንደ ክልል ከገጠመን ሐዘን ፈጥነን በመውጣት የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን ገልጸው የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነውን በአንድ ጀንበር 100 ቤቶች ግንባታ መጀመሩን አመላክተዋል።
 
ይህ ተግባር ከተባበርንና ከተቀናጀን የማንሻገረው ፈተና አለመኖሩን አመላካች ነው ያሉት አቶ ጥላሁን ዛሬ "በጉርዳ" አካባቢ የቤት ግንባታ ከማስጀመር ባሻገር የቋሚ ሰብሎች ችግኝ ተከላ እንደሚከናወንም አመላክተዋል።
 
በቀጣይ በአካባቢው ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ ተቋማት ለማሟላት በተለመደው ቅንጅት መረባረብ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
 
በመርሃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ አካባቢዎች የተገኙ የልማት አጋሮችን ማመስገናቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top