በፍትህ ተቋማት እና ፍርድቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተገልጋዮች ለኢቲቪ ገልጸዋል።
የዳኝነት ችግር፣ የፋይል አያያዝ፣ የቀጠሮ ቀን ያለአግባብ ማራዘም፣ በጉዳዮች ውስጥ ጉዳይ አስፈፃሚ እንዲገባ ምቹ እድል መፍጠር እና ሌሎችም መሰል ችግሮች የፍትሕ መጓደል እንዲፈጠር ምክንያት መሆናቸውን ተገልጋዮቹ ጠቅሰዋል።
በመንግስት የሪፎርም መርሐ ግብር ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራባቸው ከሚገኙ ተቋማት መካከል የፍትሕ ተቋማት መካተታቸው ይታወቃል።
በዚህም ፍትሃዊ፣ ተዓማኒ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የቀረፈ አሰራር ለመተግበር የተጀመሩ ስራዎች ከምን ደረሱ? ሲል የኢቢሲ አዲስ ቀን ሾው 'የሀገር ጉዳይ' አድርጎ ተመልክቶታል።
ባለፉት 5 ዓመታት ለለውጡ መሰረት የሚሆኑ ሕጎች እና አሰራሮችን ማሻሻል እና ማጠናከር ላይ እየተሰራ መሆኑን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንት አበባ እምቢአለ ለኢቲቪ ገልጸዋል።
በ5 ዓመት ፍኖተ ካርታ የትኩረት አቅጣጫ መሰረት የዳኝነት ነፃነት፣ተደራሽነት እና የአገልግሎት ጥራት ላይ የሚያተኩሩ ሕጎች ላይ ማሻሻያ መደረጉንም አንስተዋል።
ይህም ፍርድ ቤቶች በሕገ-መንግስቱ በተዘረጋው አግባብ መሰረት የራሳቸውን በጀት አቅርበው የሚያስወስኑበት እንዲሁም የራሳቸውን ሰራተኛ ራሳቸው የሚቀጥሩበት አሰራር ከማሻሻያው የሚጠቀሱት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በዳኞች ተጠያቂነት ላይ የሚያተኩር የዲሲፕሊን ደንብ ማሻሻያ በሦስቱም የፍርድ ቤት ደረጃ የኢንስቴክሽን ስራ ማጠናከር፣ የመዝገቦች ኦዲት፣ ተገልጋዮች የቅሬታ ጥቆማ የሚያቀርቡበት የዲጅታል ሲስተም የማሻሻያው አካል መሆናቸውን ምክትል ፕሬዝደንቷ ጠቅሰዋል።
የሕግ አተረጓጎም እና አረዳድ፣ በጉዳዮች ላይ ወጥ የሆነ እና ተገማች ውሳኔ የመስጠት አቅም እና የሕግ መተንተን አግባብ የፍትሕ መጓደልን እንሚያስከትሉ በመረዳት ይህን የሚቀርፍ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ለተገልጋዮች ቅሬታ መስጫ መንገድ ቢበጅም በአገልግሎቱ የሚመጣ ቅሬታ እና እስከመጨረሻ የመከታተል ክፍተት በተገልጋዩች ዘንድ መኖሩን አመላክተው፤ ብልሹ አሰራሮችን አንጥሮ ማውጣት ለማህበረሰቡ የቀረበ በመሆኑ በዚህ ሂደት ውስጥ ማህበረሰቡ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
በሚደረጉ ማሻሻያዎች ክፍተቶችን ለመሙላት አሁንም እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቷ፤ ተገልጋዮች ያሏቸውን ቅሬታዎች በፅሑፍ እና በመልዕክት ማስገባት እንደሚችሉ ገልፀዋል።