አፄ ምኒልክ በአዳራሹ፣ እቴጌ ጣይቱ በዕልፍኝ ባለሟሎችን እና ወየዛዝሩን ይዘው ግብሩ አንድ ቀንም ሳይጓደል ይዘምታሉ።
ከዘመቻው ላይ ጠጁ፣ ማሩ አለመጉደሉ ስለምንድን ነው? ያልክ እንደሆን ይህንን ታሪክ መመልከት ነው።
በስድስት ድንኳን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር፤ በአራት ድንኳን ወጡ ሲሠራ ሲያድር፣ ጠጁ በቀንድ፣ በኮዳ ደግሞ ሦስት መቶ፣ ስድስት መቶ የሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ፣ ግብሩ ይጎድል ይመስልሃል” በማለት ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ወልደአረጋይ የሴቶችን የዓድዋ ጦርነት ላይ ያበረከቱትን ሚና ያነሣሉ።
ለፓን አፍሪካኒዝም መጠንሰስ መነሾ እና ማንቂያ ደወል የሆነው የዓድዋ ድል ምሉዕ እንዲሆን ሴቶች ባላቸውን፣ ወንድማቸውን፣ አባታቸውን ወኔ አስታጥቀዋል፤ ልብ አቀብለዋል።
በቀደመው ጊዜ ነጭ የሚከበርበት እና ያለው ሁሉ ይደረግ የነበረውን ሥርዓት እቴጌ ጣይቱ “እኔስ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ውል ከመቀበል ሞቴን እመርጣለሁ” በማለት ለመጀመሪያ ጊዜ የደፈሩ እና ለጦርነት ውረድ እንውረድ የተባባሉ ጀግና እንስት ናቸው።
እኝህ በዘመኑ ያልተጨቆኑ እና የሚያነሱት ሐሳብ የሚከበርላቸው ንግሥት 12 ሺህ የሚሆኑትን እንስቶች ጋሻ፣ ጦር እና ጎራዴ እንዳስታጠቋቸው የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ።
እንዲሁም ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች ይዘው እንደዘመቱም መረጃዎች ያመላክታሉ።

እነዚህን ሴቶች እቴጌ ጣይቱ የንጉሣዊ ቤተሰብ፣ የአገልጋይ፣ የሹማምንት፣ የወታደር ሚስት እንዲሁም እቁባት ብሎ በመከፋፋል ይዘው የሄዱ ሲሆን ይህም ማንኛውም ተዋጊ ከጦርነቱ በፊት ከነበረው ልምድ እንዳይጎድልበት እና እንዳይከፋው ብሎ በማሰብ ነበር።
በተጨማሪም ጠላ ጠማቂ፣ ጠጅ ጣይ፣ ወጥ ሰሪ፣ እንጀራ ጋጋሪ፣ ገንቦኛ እንዲሁም ቀስቃሽ ብሎ በቡድን በመመደብ ለሁሉም ኃላፊነት የተሰጠበት እንደነበር ያነሣሉ።
ተዋጊዎቹ እንዳይጎድልባቸው የመንከባከብ፣ እንዳይራቡ የመመገብ፣ እንዳይሰንፉ የመቀስቀስ ማለትም የሴቶቹ በጦርነቱ ቦታ መገኘት የዓይነ እርግብ ወይም በእነርሱ ፊት ተሸንፎ ላለመታየት በማሰብ ወደ ኋላ ሳያፈገፍጉ ደፍረው እንዲዋጉ የማድረግ፣ የማስደሰት ሚና ነበራቸው።
እንዲሁም በባህላዊ የሕክምና ጥበብ ቁስለኛ የማከም ኃላፊነትን የተወጡ ሲሆን የተጎዱትን ሲያክሙ ኢትዮጵያዊ ወይም ጣሊያናዊ ሳይሉ የሰው ዘር የሚለውን በማስቀደም ከሁለቱም ወገን የተጎዱትን ሲያክሙ፣ የሞቱትን አፈር ሲያለብሱ እንደነበርም ይገለጻል።
ወርሃ የካቲት ለጦርነት ከተመረጠበት አንዱ ምክንያት ባለው የነፋሻማ አየር ጭምር ነውና እንስቶቹም ይህን በመጠቀም የጠላት መንደር ላይ የሰደድ እሳት ለቅቆ በማጋየት፣ የተመከረውን በመሰለል፣ የጠላትን የመገናኛ መስመሮች በተለይም የቴሌግራም መስመሮች በመበጣጠስ፣ በጦፈው ውጊያ ውስጥ እየተሸከለኩ ጥይት በማቀበል፣ እንዲሁም መሪ ከፊት ሲሞት ተከታይ ወደ ኋላ እንዳይሸሽ ብሎ በማሰብ ከፊት በማበርታት ባስ ሲል ቃታም እየመዘዙ ሲዋጉ እና ሲያዋጉ እንደነበር ታሪክ ያወሳል።
በጦርነቱ ወቅት ጣሊያን ከሠራው የ70 ሜትር ርዝመት ካለው ምሽግ የሚሰነዘረው የጥቃት ብልጫ ሽንፈት እንዳያስከትል በማሰብ በቦታው ያለውን “ማይአንሽቲ” የተባለውን የውኃ ምንጭ የመቆጣጠር ስልትን ተጠቅመዋል።
ይህም ጠላት ከቦታው እንዲያፈገፍግ ያደረገ ነው።
በዓድዋ ከጦር መሣሪያው ባልተናነሰ መለኮታዊ ስካርን አላብሶ የሚገፋው የሴት አዝማሪዎች ሽለላ እና ቀረርቶ ከጦርነቱ በኋላ ይሁን የተባለ እና አዝማሪዎቹንም ለደጅ አዝማችነት ክብር ያበቃ ሆኖ አልፏል።
በዚህም ሴቶቹ በዓለም ላይ ጥቁር እና ነጭ እኩል ነው የሚለውን እሳቤ መሬት እንዲረግጥ ባደረገ ድል ላይ አሻራቸውን አኑረው ማለፋቸውን ያሳየናል።
በአፎሚያ ክበበው