ሁላችንም የዓድዋ ውጤት ነን

7 Days Ago 1081
ሁላችንም የዓድዋ ውጤት ነን

ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ሊወርር እና ቅኝ ሊገዛቸው የመጣውን የጣሊያን ጦር በሀገር ፍቅር ወኔ አሳፍረው ከመለሱ 129 ዓመታት ሆነ።

ያ አስደናቂ ድል በመላው ዓለም በተለይም ደግሞ በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ሲዘከር ይኖራል።

ለመሆኑ የአሁኑ ትውልድ የዓድዋን ድል እንዴት ይገልጸዋል? ሲል “ኢትዮጵያዊነት እና አፍሪካዊነት በእኔ ትውልድ” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት ያዘጋጀው ውይይት ተሳታፊዎችን ጠይቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪው ደቻሳ አበበ (ዶ/ር)፣ “ዓድዋ የሚወዱን እና የሚያደንቁን ብቻ ሳይሆኑ ጠላቶቻችንም የመሰከሩለት ታላቅ ድል ነው” ብለዋል። 

ራሳቸውን የዓለም ፈጣሪ አድርገው ይቆጥሩ የነበሩ ምዕራብያዊያንን በመቃወም የጥቁር ሕዝቦችን የበታችነትን መቀልበስ እንደሚችሉ ያመላከተ ታላቅ ምልክት ስለመሆኑም ተናግረዋል። 

"ሁላችንም የዓድዋ ውጤት ነን፤ የዛሬ መሠረታችንም ዓድዋ ነው” የሚሉት ተመራማሪው፣ ታሪካዊ ገጠመኞቻችን እና ድሎቻችንን ጠብቀን ሊቀጥል በሚችል መልኩ ለመጪው ትውልድ ማቀበል እንዳለብን መክረዋል።

ታሪክ እና ትውልድ የዱላ ቅብብል በመሆኑ ዓድዋን ከሳጥን ውጪ ማሰብ እንደሚጠበቅብንም አመላክተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት ተማሪ የሆነችው ማህሌት መኮንን በበኩሏ፤ ዓድዋ ነጮች አንገታቸውን የደፉበት እንዲሁም ኢ-ፍትሐዊ የሆነውን የሰው ልጆች በደል እና የጭቆና አሠራር የከሸፈበት ነው ስትል ገልጻለች። 

ዛሬ ላይ "እኛ" ብለን ለማውራታችን እንደ አፍሪካ ምሳሌ የሆንበት፣ አንገታችንን ቀና አድርገን በኩራት የቆምንበት እና ከሰው እኩል መሆናችንን ያስመሰከርነው  በዓድዋ ድል  ምክንያት ነው ትላለች። 

የጥቁር ሕዝቦች አርማ የሆነው ዓድዋ የሚዘከር ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ላይ  አለ ስትልም ተማሪዋ ተናግራለች።

በዩኒቨርሲቲው የማስተርስ ትምህርት ተማሪ የሆነው ሙሉጌታ አጥናፍ ደግሞ፣ "ዓድዋ በሌሎች ሀገራት ፊት የሚያቆመኝ እና የሚያኮራኝ ታሪክ ነው" ሲል በኩራት ይገልጻል።

ዓድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የድል ማህተም እንደሆነ እና በኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካዊያን ጭምር የተለየ ኩራት የሚሰጥ ስለመሆኑም ነው የገለጸው።

ታምሩ ውዴ የ2ኛ ዓመት ተማሪ ሲሆን "ዓድዋ ለእኛ ሕይወታችን ነው" ሲል ገልጾ፣ “ዓሣ ከውኃ ሲወጣ መኖር እንደማይችለው ሁሉ እኛም ከዓድዋ መንፈስ ስንወጣ ብዙ ነገራችን የሚሞት ነው” ሲል የድሉን ታላቅነት አብራርቷል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ አንድነት መንፈስ ባህላችንን እና ታሪካችንን ልንጠብቅ ይገባል ሲልም ለአሁኑ ትውልድ መልዕክት አስተላልፏል።

ይህ ትውልድ የዓድዋ ባለ አደራ በመሆኑ ይህንን አደራ፣ ታሪኩን እና ማንነቱን በአንድነት መንፈስ በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ሊያሻግር ይገባል ሲልም መክሯል።

በሜሮን ንብረት


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top