የኢትዮጵያ አየር ኃይል አልሸባብ ላይ ጥቃት ማድረሱን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ

16 Days Ago 557
የኢትዮጵያ አየር ኃይል አልሸባብ ላይ ጥቃት ማድረሱን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሶማሊያ በማዕከላዊ ሸበሌ ክልል በሚንቀሳቀሰው የአልሸባብ ቁልፍ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ማድረሱን የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃድር ሞሐመድ ኑር አስታውቀዋል።
 
መከላከያ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የአልሸባብ ጠንካራ ይዞታዎችን አውድሟል።
 
ከአንካራው ስምምነት በኋላ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ያለው የፀጥታ ትብብር እየተጠናከረ መምጣቱን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ይህ የአየር ጥቃትም ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሸባሪ ቡድኑ ላይ የወሰደችው ከፍተኛው እርምጃ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
 
እርምጃው የተወሰደው አሸባሪው ቡድን ከሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጋቸው ተከታታይ ውጊያዎች በኃይል በያዛቸው የማዕከላዊ ሸበሌ ክልል መሆኑ ተጠቅሷል።
 
የሽብር ቡድኑ ወደ ሞቃዲሾ እየተቃረበ መምጣቱን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ ስጋት የፈጠረባቸው ሀገራት ወደ ሞቃዲሾ የሚደረገውን የአየር በረራ አቋርጠዋል።
 
ከአንካራው ስምምነት ወዲህ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ሶማሊያን የማረጋጋት ተልዕኮ (AUSSOM) ወስጥ ተሳትፎዋን እንድትቀጥል የሶማሊያ መንግሥት ዕውቅና መስጠቱን የጠቀሰው የጋርዌ ኦንላይን ዘገባ፤ የኢትዮጵያ ወደ ሰላም ማስከበሩ ሂደት መመለስ አልሸባብን ለመዋጋት በጣም አስፈላጊ ነው ብሏል።
 
የሁለቱ ሀገራት መከላከያ ኃላፊዎች በሞቃዲሾ በተገናኙበት ወቅት፣ የጋራ የፀጥታ ኃይልን በማጠናከር አካባቢውን ከአሸባሪው አልሸባብ ለማፅዳት መስማማታቸው በዘገባው ተጠቅሷል።
 
በለሚ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top