12ቱ የዓድዋ ጦር ጀኔራሎች፤ የአንድነት እና የነጻነት ችቦ አብሪዎች

9 Days Ago 3489
12ቱ የዓድዋ ጦር ጀኔራሎች፤ የአንድነት እና የነጻነት ችቦ አብሪዎች

ዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክሩለታል። ሌሎች የአውሮፓ ወራሪ ኃይሎች እንዳደረጉት ሁሉ የጣሊያን ወራሪ ኃይልም ኢትዮጵያን ቅኝ ሊገዛ ባሕር አቋርጦ፣ ድንበር ጥሶ መጣ።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዘመነ መንግሥታቸው ሀገራቸውን ቅኝ ሊገዛ የመጣውን ወራሪ ኃይል እንዲመክቱ መላ ኢትዮጵያውያንን ያንቀሳቀሰ ጥሪ በማድረግ እና በማስተባበር ዘመቱ።

ሀገሬው ሁሉ “እምቢኝ ለሀገሬ! እምቢኝ ለኢትዮጵያ!” ብሎ ኑሮውን፣ ሚስቱን እና ልጆቹን እርግፍ አድርጎ ጥሎ ወደ ዓድዋ ዘመተ።

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ከወራሪው ጣሊያን ጋር የማይነጻጸር የጦር መሣሪያ ቢታጠቁም ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር እና ለራሳቸው የሚሰጡት ክብር ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ኃይል እንዲያሸንፉ ስንቅ ሆናቸው።

ጠላትንም ድል ነሡ! እዚህ ላይ ታዲያ ያልሰለጠና እና ዘመናዊ ጦር ሳይገነቡ የሀገራቸውን ፍቅር ብቻ ታጥቀው የዘመቱትን ኢትዮጵያዊ በመምራት ደማቅ ታሪክ የጻፉ 12ቱን የጦር ጄኔራሎች ታሪክ ማንሣት ግድ ይላል።

እነዚህ 12 ጄኔራሎች እነ ማን ናቸው? ለዛሬውስ ትውልድ ምን አስተማሩ? እነሆ!

• ፊታራሪ ገበየሁ ገቦ ጉርሙ - (አባ ጎራው)፤ የትውልድ ዘመን - ያልታወቀ

• ልዑል ራስ መኮንን ወልደ ሚካኤል ጉዲሳ - (አባ ቃኘው) የትውልድ ዘመን - 1844-1898

• ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ተሰማ ጎሹ - (አባ ጠና)፤ የትውልድ ዘመን - 1842 -1893

• ንጉሥ ሚካኤል አሊ ሊበን - (አባ ሸንቆ)፤ የትውልድ ዘመን - 1840/43- 1911

• ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮባ - (አባ ነፍሶ)፤ የትውልድ ዘመን - 1854-1929

• ራስ ወሌ ብጡል ኃይለማርያም - (አባ ጠጣው)፤ የትውልድ ዘመን - 1835 -1910

• ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲንግዴ ሁንዱል - (አባ መቻል)፤ የትውልድ ዘመን - 1846-1919

• ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ - (አባ ነጋ)፤ የትውልድ ዘመን - 1840-1891

• ራስ መንገሻ ዮሐንስ ምርጫ - (አባ ግጠም)፤ የትውልድ ዘመን - 1857 - 1898

• ዋግሹም ጓንጉል ብሩ ገብረ መድኅን - (አባ መርከብ)፤ የትውልድ ዘመን - ያልታወቀ

• ራስ አባተ ቧያለው ንጉሡ - (አባ ይትረፍ)፤ የትውልድ ዘመን - 1861- 1910

• ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ቢተርፍ - (አባ ገድብ)፤ የትውልድ ዘመን - ያልታወቀ

እነዚህ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተውጣጡ የጦር መሪዎች በአርበኝነት እና በጀግንነት በዓድዋ ጦርነት ላይ ተዋግተው እና አዋግተው በቅኝ ገዢ ኃይሎች ላይ የመላው የጥቁር ሕዝቦች አሸናፊነት ፋና ወጊ የሆነውን የዓድዋ ድልን አጎናፅፈውናል።

በዓድዋ ጦርነት የተሳተፉት እነዚህ የጦር መሪዎች በታላቅ ድላቸው በዓለም መድረክ ለጥቁር ሕዝቦች አዲስ አመለካከት እና ግንዛቤ ፈጥረዋል።ታላቅ አርበኝነታቸው፣ በከፍተኛ ኃላፊነት እና በአንድነት መሰለፋቸው፣ ብልህነት የተሞላበት የጦር አመራር ክህሎታቸው በቅኝ ገዢ ኃይሎች ፊት በአሸናፊነት እንዲቆሙ አስችሏቸዋል።

የመሪዎች ጀግንነት እና ፅናት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አልፎ በመላው ዓለም የሚገኙ የጥቁር ሕዝቦችን የአሸናፊነት መንፈስ ያላበሰ ነበር። የአንድነት እና የነፃነት ቀንዲል የሆኑት የእነዚህ ጄኔራሎች ታሪክ ለመላው አፍሪካውያን እና የጥቁር ሕዝቦች መነቃቃትን የፈጠረ ነው።

የእነዚህ የጦር መሪዎች ቅንጅት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባሻገር በጋራ አሸናፊ የመሆን ተምሳሌት ለመሆን አብቅቷቸዋል። በጀግንነት፣ በጥበብ እና በመፍትሔ አመንጪነት የሚታወቀው የጋራ ታሪካችን ለዛሬው ትውልድም መሠረት የሚሆን ነው።

ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በአንድነት በመዝመት ጠላትን ድል እንዳደረጉት ጀግኖች አባቶቻችን የዛሬውም ትውልድም የዓድዋን መንፈስ ተላብሶ ሀገሩን ከድህነት እና ኋላ ቀርነት እንዲሁም ከውጭ ጥገኝነት የማላቀቅ ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል።

በኔፍታሌም እንግዳወርቅ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top