ኢትዮጵያ አብዛኛው ታሪኳ የጦርነት ነው፡፡ ራስን የመከላከል ጦርነት፡፡ የአትንኩኝ እና የፀረ ወረራ ጦርነት! በአክሱማውያን ዘመን የፐርሺያ ተስፋፊዎችን ከመከላከል ጀምሮ እስከ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ የዚያድ ባሬ ወረራ ድረስ ያሉ ጦርነቶችንም በድል አጠናቀቃለች፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን ጦርነቶች ያደረገቸው የማንንም ድንበር ተጋፍታ፣ የማንንም ሀብት ፈልጋ ሳይሆን ድንበሯን ገፍተው፤ ሉዓላዊነቷን ተዳፍረው የመጡባትን ለመመከት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል ባስተላለፉት መልዕክት ላይ እንደጠቀሱት፤ ኢትዮጵያውያን ጦርነት ምን እንደሆነ ስለሚያውቁ ይፈሩታል፤ ይሸሹታልም፤ ገፍቶ የመጣ ካለ ግን ለሰላማቸው ሲሉ ተዋግተው ያሸንፉታል፡፡
ከዛሬ 47 ዓመት በፊት በተደረገው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ጦርነት ወቅትም የታየውም ይኸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምታምነው የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ከጉርብትና የላቀ የደም፣ የሃይማኖት እና የባሕል ትስስር ያላቸው ሕዝቦች እንደሆኑ ነው፡፡ ይህን እውነታ የካዱ የሶማሊያ መሪዎች ግን "ታላቋ ሶማሊያ" የሚል ህልም ይዘው እስከ አዋሽ ያለውን የኢትዮጵያን ግዛት የመጠቅለል ዓላማ ይዘው ሲዘጋጁ ቆይተው ከ1960ዎቹ አጋማሽ የጀመሩትን ትንኮሳ በ1968 ዓ.ም ሙሉ ወረራ ፈጸሙ፡፡
በዚያድ ባሬ የሚመራው የያኔው የሶማሊያ መንግሥት ወረራውን አጠናክሮ በደቡብ ምሥራቅ እስከ 300 ኪሎ ሜትር፣ በምሥራቅ ደግሞ እስከ 700 ኪሎ ሜትር የኢትዮጵያን ግዛት ያዘ፡፡
በወቅቱ በመንግሥት ለውጥ ምክንያት በውስጥ አጀንዳዋ ተወጥራ የነበረችው ኢትዮጵያ ወረራውን ፈጥና ለመቀልበስ አልቻለችም፡፡ ወራሪው የዚያድ ባሬ መንግሥት የኢትዮጵያን ግዛት እንዲለቅ በወዳጅ ሀገራት አማካኝነት ቢጠየቅም የልብ ልብ የተሰማው ወራሪ ግን ይበልጡኑ ወደፊት ገፍቶ መጣ፡፡ ይባስ ብሎም ኢትዮጵያ በወቅቱ የምትከተለውን የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ያደረገችው አሜሪካ ኢትዮጵያ በራሷ ገንዝብ የገዛቻቻውን የጦር መሣሪያዎችን ከመከልከሏም በላይ የጦር መሣሪያ ግዢ ማዕቀብም ጣለችባት፡፡
በድርድር ለውጥ እንደማይመጣ የተረዳችው ኢትዮጵያም በአጭር ጊዜ ዝግጅት ኃይሏን አዘጋጅታ ወረራውን የመቀልበስ ፍልሚያውን ጀመረች፡፡ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሀገር መወረሯን ጠቅሰው ባቀረቡት የክተት ጥሪ የሀገሩን ነጻነት ከምንም በላይ የሚያስቀድመው ኢትዮጵያዊ ከወጣት አስከ አረጋዊ ዘምቶ ሀገሩን ለማስከበር ቆረጠ፡፡ እናቶች ስንቅ ማዘጋጀቱን ተያያዙት፣ ለዘመቻ የተመዘገቡት በሦስት ወራት ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ግንባር ዘመቱ፡፡ የሰውን የማይፈልጉት ነገር ግን ገፍቶ የመጣባቸውን ለመመከት ለሕይወታቸው የማይሰስቱት ኢትዮጵያውያን በካራማራ ላይም በደማቸው ማኅተም ሀገራቸውን አስከበሩ፡፡
የወራሪ ራስ ምታት የነበሩት የሰማይ ነብሮች በሰው ኃይልም ሆነ በትጥቅ ለረጅም ጊዜ ዝግጅት በማድረግ ኢትዮጵያን የወረረውን የዚያድ ባሬን ኃይል ለማሸነፍ ሚናቸው እጅግ የላቀ ነበረ፡፡
በጥቂት እና ኋላ ቀር የውጊያ አውሮፕላኖች፣ ነገር ግን የአባቶቻቸውን ወኔ ከልዩ ብቃት ጋር ያጣመሩ የሰማይ ነብሮች ለወራሪው የራስ ምታት ሆነዋል፡፡ ኦስትሪያዊው የጦር ተንታኝ እና የታሪክ ተመራማሪ ቶም ኩፐር "Wings over Ogaden: the Ethiopian-Somali war, 1978-79" በሚለው መጽሐፋቸው የወራሪውን ህልም መና ያስቀረውን የአየር ኃይሉ ሚና እና የአብራሪዎቹን ጀግንነት በዝርዝር አቅርበዋል። ጀግናው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጠቅላላው የሶማሊያ ጦርነት ወቅት ለወሳኙ ድል መገኘት በጣም ቁልፍ ሚና ነበረው።
የኢትዮጵያን ሰማይ ከሶማሊያ ጄቶች በማጽዳት ለምድር ኃይሉ ደጀን ለመሆን ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ፣ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ፣ ኮሎኔል መንግስቱ ካሣ፣ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ፣ ብ/ጄኔራል አሸናፊ ገ/ፃዲቅ እና መቶ አለቃ አፈወርቅ ኪዳኑ ለአየር ላይ ውጊያ፤ ሜ/ጁኔራል አመኃ ደስታ፣ ብ/ጄኔራል ተጫኔ መስፍን፣ ኮሎኔል ብርሃኑ ውብነህ፣ ኮሎኔል ብርሃኑ ከበደ፣ ኮሎኔል ተሻለ ዘውዴ፣ ብ/ጄኔራል ንጉሤ ዘርጋው እና ብ/ጄኔራል ተስፉ ደስታ የ5ኛው ስኳድሮን ቦምብ ጣይ በራሪዎች፣ አንዲሁም ብ/ጄኔራል መስፍን ኃይሌ እና ኮሎኔል አሰፋ መክብብ B-52 ቦምብ ጣይ ካምቤራ ላይ ተመድበዋል፡፡
የዚያድ ባሬ ወራሪዎች ገፍተው በመምጣት ድሬዳዋ ድረስ ገብተዋል፡፡ የሶማሊያ ጄቶች የኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በመግባት በዓለም አቀፍ የአቪየሽን ሕግ ክልክል የሆነውን የሲቪል አውሮፕላት መትተው ጣሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሰማይ ላይ ነብሮች ይህን ሲያመለከቱ ከራዳር መልዕክት እየተቀበሉ የኢትዮጵያን ሰማይ ማስከበር ጀመሩ፡፡
የ9ኛው ሥልታዊ ተዋጊ ስኳዶሮን አውሮፕላኖች መሉ በሙሉ ሰማይ ላይ በማንዣበብ /CAP- Combat Air Patrol/ የኢትዮጵያን አየር ክልል እንዲጠብቁ ተደረገ፡፡ በተለይም የትራንስፖርት አውሮፕላኖች፣ የተዋጊ አውሮፕላን ሽፋን ካላገኙ በስተቀር እንዳይበሩ ተወሰነ፡፡ ሐምሌ 17 ቀን 1969 ዓ.ም ሁለት የሶማሊያ ተዋጊ አውሮፕላኖች ዳግመኛ የኢትዮጵያን የሲቪል አውሮፕላን ለመምታት ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል መብረር መጀመራቸውን የራዳር መልዕክት መጣ፡፡
ኮሎኔል መንግሥቱ ካሣ እና በኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ‘F-5E’ ጄቶቻቸውን እያበረሩ ወደ ቦታው አመሩ፡፡ ኮሎኔል በዛብህ አንዱን ሚግ በሚሳኤል መትተው ጣሉት፣ ይህንን ያየው ቀሪው ሚግ ፍጥነት ጨምሮ ውጊያውን አቋርጦ ወደ ሀርጌሳ አመራ፡፡ የሚጉ ፍጥነት ከ‘F-5E’ የተሻለ በመሆኑ የሶማሊያው አብራሪ አመለጠ፡፡ ኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ኢትዮጵያን ሊደፍር የመጣውን ጄት በመጣል የመጀመሪያውን ግዳይ ጣሉ፡፡
ሐምሌ 18 ቀን 1969 ዓ.ም ደግሞ ብዛት ያላቸው የሶማሊ አየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች ጠረፍ አቋርጠው የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሰው ሲገቡ የራዳር መልዕክት ደረሰ፡፡ ብ/ጄ ለገሠ ተፈራ፣ ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ እና መቶ አለቃ አፈወርቅ ኪዳኑ ወደ ቦታው ተላኩ፡፡ ብ/ጄኔራል ለገሠ የሚመሩት ይህ የበረራ ቡድን ሶማሌዎቹን ከፊት እና ከኋላ ከታች እና ከላይ ሲያዋክቧቸው አራቱ የሶማሊያ ሚግ-21 ተዋጊ አውሮፕላኖች መሪ እና ተከታዩ ግራና ቀኝ ተለያይተው መዞር ሲጀምሩ ኢትዮጵያውያኑ ከፍታ እየጨመሩ ፍጥነት እየቀነሱ አብረዋቸው መዞር ላይ እንዳሉ ሁለቱ ሚጎች እርስ በርስ ተጋጩ፡፡ የቀሩትን ሁለት ሚግ-21 ጄቶችን ለመጣል ለገሠ ተፈራ ወደ አንዱ በመቅረብ ተኩሰው ጣሉት፡፡ ባጫ ሁንዴ እና አፈወርቅ ኪዳኑም የቀረውን ሚግ እየተከተሉት እያለ የሶማሊያው ሚግ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ በራሱ ጊዜ ወድቆ ተከሰከሰ፡፡
ብ/ጄ ለገሠ ይህን ግዳይ ከጣሉ በኋላ ሌሎች ሁለት ሚግ - 17 ተዋጊ አውሮፕላኖች አግኝተው ሁለቱንም በአየር ላይ በሚሳኤል መትተው ጣሏቸው፡፡ ይህም ሶማሊያ ለብዙ ጊዜ ስትዘጋጅባቸው የነበሩት ተዋጊ አውሮፕላኖቿ እንዲሳሱ ከማድረጉም በላይ የቀሩትም ለግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩ ብርክ እንዲይዛቸው አደረገ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ነብሮች በኢትዮጵያ አየር ክልል ብቻ ሳይወሰኑ ወደ ሶማሊያ አየር ክልል በመግባት አውሮፕላኖቹ ከመደባቸው ሳይነሱ ባሉበት ሊመቷቸው ችለዋል፡፡
እነዚህ የቁርጥ ቀን ጀግኖች ለራሳቸው ሳይሳሱ የኢትዮጵያን ክብር፣ ልዕልና፣ አንድነት እና ሉዓላዊነት አስጠብቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የታደለች በመሆኗም አለቀላት በተባለበት ጊዜ ሁሉ አለንልሽ የሚሏት፣ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የሚያስከብሯትን ልጆች አጥታ አታውቅም፡፡
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬም ለወገኖቹ መከታ፣ ኢትዮጵያን በክፉ ለሚያስቧቸው ደግሞ የቀን ቅዠት ነው፡፡ "ሰማዩ የኛ ነው!" የሚለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል እንደ መሪ ቃሉ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝነት እየጠበቀ ይገኛል፡፡ ራሱም እያመረተ ጭምር ዘመኑ ያፈራቸውን ትጥቆች የታጠቀው አየር ኃይሉ ማንኛውንም ትንኮሳ የሚመክት እና የኢትዮጵያ ጠላቶች ደጋግመው እንዲያስቡበት በሚያደርግ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አየር ኃይሉ በጦርነት ወቅት ማሸነፍ እና ማውደም የሚችል ስትራቴጂክ አቅም በመፍጠር ረገድ አመርቂ ውጤቶችን አስመዝግቧል። አስተማማኝ የደህንነት ዋስትናነቱ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድም ጭምር መሆኑን በሶማሊያ ውስጥ በአልሸባብ ላይ እየወሰደው ባለው እርምጃ አረጋግጧል፡፡
በአስቸጋሪ ወቅት እና ጊዜ ሁሉ የሀገሩን የአየር ድንበር የሚጠብቁ እና ጠላትን በአየር ላይ ማስቀረት የሚችሉ የአባቶቻቸው ወኔ ወራሽ የሆኑ እብራሪዎችን እና ሙያተኛን አደራጅቶ እየዘመነም ነው።
በለሚ ታደስ