የአባቶቻቸው ወኔ ወራሽ የወራሪዎቹ ራስ ምታት - ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ

16 Days Ago 418
የአባቶቻቸው ወኔ ወራሽ የወራሪዎቹ ራስ ምታት - ኮሎኔል ባጫ ሁንዴ

ከ1969 ዓ.ም እስከ 1970 ዓ.ም ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር በአየር ላይ በተደረገው ጦርነት እና ለእግረኛው ተዋጊ በተለያዩ ቀናት የተኩስ ድጋፍ በማድረግ በአየር ላይ የሶማሊያን ሚግ ተዋጊ አውሮፕላኖች ከኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አጽድተዋል።

በግዳጅ ላይ እያሉ አውሮፕላናቸው ከምድር በተተኮሰ ሮኬት ተመትቶባቸው በፓራሹት መውረድ ባለመቻላቸው በአንድ ሞተር ብቻ ጄታቸውን ለማሳረፍ የቻሉ ብቁ እና ቆራጥ አብራሪ ነበሩ።

ሙያን በልብ ያሉ ብዙ የማያወሩ ቅን እና ጠንካራ ሠራተኛ፣ ሙያቸውን የሚያከብሩ፣ በባልደረቦቻቸው እና በኃላፊዎቻቸው ዘንድ እጅግ የተወደዱ እንደሆኑ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።

ብዙ ግርግር የማያበዙ እና ታላቅ ጀብዱ ፈጽመው ሲመለሱ እንኳን መጽሐፍ ወደ ማንበብ የሚሄዱ ዝምተኛ እንደሆኑ በቅርብ የሚያውቁአቸው ጓደኛቸው እና የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ብርሃኑ ከበደ ያወሳሉ።

በላቀ የጀግንነት ተግባራቸውም ከወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም እጅ የላቀ የጦር ሜዳ ሜዳይ ተሸልመዋል።

የዛሬው የዐውደ ሰብ ባለተራችን ኮለኔል ባጫ ሁንዴ በ1937 ዓ.ም ነው በጊንጪ ከተማ የተወለዱት። ትምህርታቸውን በአምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቅቀዋል። በ1957 ዓ.ም በአውሮፕላን መካኒክነት ሙያ አየር ኃይልን ለማገልገል ተቀጥረው ሥልጠናቸውን በላቀ ብቃት ጨርሰዋል።

ሥልጠናቸውን እንደጨረሱ ያመጡት ውጤት የላቀ በመሆኑ እና በመምህራኖቻቸው ከፍተኛ ተወዳጅነት ስለነበራቸው ወደ አብራሪነት እንዲገቡ ተደረጉ። እርሳቸውም አውሮፕላን አብራሪ ለመሆን ፍላጎት ስለነበራቸው ሙያው የሚጠይቀውን ሥልጠና በብቃት በማጠናቀቅ አብራሪ ሆኑ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል F-5E የሚባለውን አውሮፕላን ሲገዛ ኮሎኔል ባጫ ወደ አሜሪካ ተልከው አውሮፕላኑን ማብረር የሚያስችላቸውን ሥልጠና በመውሰድ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።

እኒህ ያልተዘመረላቸው ጀግኖ በሶማሊያው ጦርነት ላይ ከፍተኛ የአየር ላይ ተዋናይ ነበሩ። የኦጋዴንን ሰማይ እንዳሻቸው እየተመላለሱበት ጠላትን አስጨንቀውታል። ሰማዩን ነግሠውበት ዚያድ ባሬ የተማመኑባቸውን እጅግ ዘመናዊ የውጊያ አውሮፕላኖችን ከሰማይ ላይ አራግፈዋል።

ልዩ የበረራ ክህሎታቸውን ከአባቶቻቸው ከወረሱት ወኔ ጋር አጣምረው ኢትዮጵያን አስከብረዋል። በአየር ለአየር ውጊያ ልዩ ችሎታ አላቸው፤ እንደነ ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ካሉት ሌሎች ጀግኖች ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአስተማማኝ ሁኔታ አስከብረዋል።

በጣም ደፋር እና ጥበበኛ ተዋጊ ነበሩ። የሶማሊያ ጦር ከምድር ወደ አየር ያስወነጭፋቸው የነበሩትን የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች እና የአየር ሙቃወሚያዎች ምንም ሳይመስላቸው በጎዴ ሰማይ ላይ ጨበጣ የመግጠም ያህል እጅግ ዝቅ ብለው በምድር ያለውን የወራሪውን ጦር ፋታ አሳጥተውታል።

ኮሎኔል ባጫ በአየር ላይ ውጊያ ሁለት የሶማሊያን ሚግ አውሮፕላኖች መትተው ጥለዋል። በከፍተኛ ደረጃ የታጠቀውን የሶማሊያን ሜካናይዝድ ጦር እየደበደቡ በትነውታል። ሃርጌሳ ድረስ በመግባት የዚያድ ባሬን የትጥቅ እና ስንቅ ማከማቻ አደባይተው የጠላትን የኋላ ደጀን ቀራርጠዋል።

በጦርነቱ ወቅት ከሰማይ ላይ እያንዣበቡ ሲጠብቁት የነበረው የኢትዮጵያ እግረኛ ጦር አባላት፡-

ሕዝባችን ከኋላ ባጫ በሰማይ ላይ እየተከተለን፣
ወደ ኋላ አንልም እናሸንፋለን፤
ዳር ድንበራችንን እናስጠብቃለን!

እያሉ ይዘምሩላቸው እንደነበር ይነገራል።

ኮሎኔል ባጫ እንደ ብ/ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሲታወሱ አብረው ስማቸው ከሚነሱት ተዋጊ ጀት አብራሪዋች ተጠቃሹ ናቸው። ዝምተኛ እና የተግባር ሰው የሚባሉት ኮሎኔል ባጫ ተልዕኮአቸውን በተሟላ ሁኔታ በመፈጸም ይታወቃሉ። ባሳዩት ከፍተኛ ጀብዱም በ1971 ዓ.ም የላቀ የጦር ሜዳ ጀብዱ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆነዋል። በ1972 ዓ.ም መጋቢት መጨረሻ በሶቬት ኅብረት ኪዬቭ ወታደራዊ አካዳሚ የፓለቲካ እና ወታደራዊ ትምህርት እንዲማሩ የተላኩትን የጦር አባላትን የቡድን መሪ በመሆን ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመልሰዋል።

በሥራቸው ላይ ነፃነት በማጣታቸውም ለነፍሳቸው ሳይሳሱ የተዋደቁላትን ሀገራቸውን ትተው በ1973 ዓ.ም ወደ ስደት እንዳመሩ ይነገራል። ዝምተኛው እና በትምህርት አቀባበላቸው ንቁ የሚባሉት ኮሎኔል ባጫ ከንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማታቸውን የተቀበሉ ጀግና ተዋጊ አብራሪ እንደነበሩ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ ኮሎኔል ብርሃኑ ከበደ በአንድ ወቅት ለኢሳት ቴሌቪዥን ተናግረው ነበር።

የሚወዱአትን፣ ሁሉንም ዋጋ የከፈሉላትን ሀገራቸውን ትተው በስደት ለመኖር የተገደዱት ኮሎኔል ባጫ በሚኖሩበት ሀገር አሜሪካ በ2007 ዓ.ም አርፈው ቀብራቸው በዚያው በስደት በሚኖሩበት ሀገር ተፈጽሟል። ቤተሰቦቻቸው በጠየቁት መሠረትም በ2015 ዓ.ም አፅማቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ እንዲያርፍ ተደርጓል።

ጥር 5 ቀን 2015 ዓ.ም አፅማቸው ወደ ኢትዮጵያ የገባ ሲሆን በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ-ፍትሐት ተደርጎለታል። በተመሳሳይ ዕለት ቤተሰቦቻቸው፣ ኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ እና የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በቢሾፍቱ አየር ኃይል የመታሰቢያ እና የጧፍ ማብራት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዶላቸዋል።

ሌ/ጄኔራል ይርማ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ጀግኖች የሚከበሩት ጀግና ትውልድ ለመፍጠር መሆኑን አውስተው፣ በሁሉም አቅጣጫ ኢትዮጵያ ጀግና አጥታ እንደማታውቅ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ለጠላት የሚያስፈራ ለወገን በሚያኮራ መልኩ እየተገነባ መሆኑንም አስታውሰዋል።

የመታሰቢያ ሥነ-ሥርዓቶቹ እንደተጠናቀቁም አፅማቸው ጥር 6 ቀን 2015 ዓ.ም በቅድስ ሥላሴ ካቴድራል ከሌሎች ጀግኖች ወንድሞቻቸው ጎን በክብር አርፏል።

በለሚ ታደሰ


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top