የእስራእል ወታደሮች ጋዛን ለሁለት ከሚከፍለዉ ኮሪደር መዉጣታቸዉ ተገለፀ

2 Days Ago 167
የእስራእል ወታደሮች ጋዛን ለሁለት ከሚከፍለዉ ኮሪደር መዉጣታቸዉ ተገለፀ

የእስራእል ወታደሮች ሰሜን ጋዛን ከደቡብ ጋዛ ከሚከፍለዉ የኖትዛሪም የጦር ቀጠና መዉጣታቸዉ ተገልጿል፡፡

የእስራኤል ወታደሮቿን የማስወጣት ተግባር ሃገሪቱ በቅርቡ ከሃማስ ጋር ባደረገችው የተኩስ አቁም ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት እየተፈፀመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የወታደሮቹ የመውጣት ውሳኔ እስራኤል እና ሃማስ አምስተኛ የእስረኞች ልውውጣቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የመጨረሻዎቹ ሶስት እስራኤላውያን ምርኮኞች እና 183 ፍልስጤማውያን እስረኞች ከተፈቱ በኋላ የተከናወነ ነው ተብሏል።

ባጋዛ ጦርነት ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የጋዛ ህንፃዎች መዉደማቸዉ የተገለፀ ሲሆን፤ 46 ሺህ በላይ የሚሆኑ ፍልስጤማዉያን መገደላቸዉ ተነግሯል፡፡

እንዲሁም 700 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት አሁን የእስራእል ወታሮች ለቀዉ በወጡት ኮሪደር በኩል ወደ ደቡብ ጋዛ ለመሸሽ ተገደዉ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡

ከስምምነቱ በኋላም ከ300 ሺህ በላይ የሰሜን ጋዛ ነዋሪዎች በጦርነቱ ተሰደውበት ከነበረው የደቡብ ጋዛ ወደ ሰሜን መሻገራቸው ተጠቅሷል፡፡

በእስራኤል እና ሃማስ ስምምነቱ መሰረት እስካሁን 16 እስራኤላዉያን ታጋቾች ሲለቀቁ፤ 566 ፍልስጤማዉያን እስረኞች ደግሞ መፈታታቸውን የዘገበው አልጀዚራ ነው፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top