በምስራቅ ሸዋ ዞን ጊምቢቾ ወረዳ አማ ቀበሌ ከሥድስት ዓመታት በፊት በዛሬዋ ቀን አስደንጋጭ ክስተትን አስተናግዳ ነበር።
ባለቤትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነው የበረራ ቁጥር ET-302 አውሮፕላን መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለመብረር በተነሳ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በመከስከሱ፤ በውስጡ የነበሩ ተሳፋሪዎች እና የበረራ ቡድን አባላት ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።
ይህንን አስደንጋጭ ክስተት ተከትሎም የአካባቢው ነዋሪዎች በኀዘን ተውጠው ነበር፡፡ ወ/ሮ ሙሉነሽ በጅጋ የአካባቢው ነዋሪ ሲሆኑ አደጋው ሲከሰት ከተመለከቱት መካከልም ነበሩ።
በአደጋው የተመለከቱት አስደንጋጭ ክስተት ከአዕምሯቸው አልወጣም ያላቸው እኚህ እናት "እነዚህ ልጆች እንደወጡ ቀርተዋል የኔ ልጆች ቢሆኑስ" በማለት በዓይን እንኳን አይተዋቸው ለማያውቋቸው ሰዎች እንደ ቤተሰብ ኀዘን ተቀምጠዋል።
በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡትም በዓመቱ የሙት ዓመት መታሰቢያ የዘከሩ ሲሆን "በሕይወት እስካለሁ ድረስም የእነዚህን ልጆች መታሰቢያ አላቋርጥም" ነው ያሉት፡፡
ወ/ሮ ሙሉነሽ በጅጋ በየዓመቱ "ያለፉትን ሁሉ ነብስ ይማርልን" እያሉ ከአካባቢያቸው ማህበረሰብ ጋር በመሆን መታሰቢያ እያዘጋጁ ቀጥለዋል።
ይህ አይነቱ ስሜት የወደቀን አይቶ ማለፍ የማይፈቅድ ማህበራዊ እሴት ያነጸው መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ።