በሶማሌ እና በአፋር ክልል ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረው ግጭት በሰላማዊ መንገድ ተፈትቶ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉን በጅግጅጋ በተዘጋጀው “ኢፍጣር ለሰላም እና ለአብሮነት” መድረክ ላይ የተገኙት ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ ተናግረዋል።
የጅግጅጋው ኢፍጣር በሁለቱ ክልል ሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት አሀድ ወይም ቃልኪዳን መሆኑንም ጠቁመዋል።
“የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በሁለንተናዊ ባህሪያቸው ተመሳሳይ ማንነት ያላቸው፣የእስልምና እምነትን የሚከተሉ፣ ብዙ የጋራ መመሳሰል እና እሴት ያላቸው በመሆኑ አፋርን እና ሶማሌን መለየት አይቻልም” ሲሉ ገልጸዋል።
አምና መሆን ከሚገባን መንገድ ወጥተን አሁን ወደ ትክክለኛው መስመር መግባት በመቻላችን እና ሰላም በመመለሱ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
“የእስልምና አስተምህሮዎች ከሥጋዊ ዝምድና ይልቅ ወንደማማችነትን ማጠናከር ያዝዛል” ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፤ ይህን በመገንዘብ ለዛሬ አብሮነት ምክንያት ለሆኑ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የትላንቱ ጥፋት የሁሉም የጋራ ጉዳት በመሆኑ የቁርሾውን ምዕራፍ ዘግተን መጓዝ ይገባል ነው ያሉት።
በሁለቱ ሕዝቦች መካከል አሁን ያለው ሰላም እንዲመጣ ድጋፍ ላደረጉ የፌዴረል መንግሥት፣ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች እና የሃይማኖት አባቶችም ምስጋና አቅርበዋል።