ከነገ ጀምሮ የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እስኪጠናቀቅ ለአሽከርካሪዎች ዝግ የሚሆኑ መንገዶች

5 Mons Ago
ከነገ ጀምሮ የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ እስኪጠናቀቅ ለአሽከርካሪዎች ዝግ የሚሆኑ መንገዶች

37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 44ኛው የሚኒስትሮች ስራ አስፈፃሚ ም/ቤት ስብሰባ በሰላምና በስኬት ለማጠናቀቅ እንዲቻል በሚከናወነው የፀጥታ ስራ እና የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ እንዲሆን አሽከርካሪዎች ሌሎች ተለዋጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠይቋል። 

የከተማውን ሰላም  ለማስጠበቅ የፀጥታ አካላት ካደረጉት ዝግጅት ባሻገር የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቁሞ፤ ህዝቡ እንደሁልጊዜው ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም እያደረገው ያለውን ድጋፍ  አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል። 

በተለይም እንግዶች ወደ ስብስባ እና ወደ ሆቴል ከሚያደርጓቸው ጉዞዎች ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ህብረተሰቡ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተገቢውን መስተንግዶ በማድረግ እንዲተባበር ጠይቋል። 

አሽከርካሪዎችም ለእንግዶቹ ቅድሚያ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆኑ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክት አስተላልፏል። 

በዚሁ መሠረት ከነገ ሐሙስ የካቲት 7 ቀን ጀምሮ ጉባኤው እስከሚጠናቀቅ፡-

  • ከፓርላማ መብራት - በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - መስቀል አደባባይ - ፍላሚንጎ - ኦምሎፒያ - ወሎ ሰፈር - ጃፓን ኤምባሲ - ፍሬንድ ሺፕ - ቦሌ ቀለበት መንገድ - ኤርፖርት
  • ከፓርላማ መብራት - በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት - ፍልውሃ - ብሔራዊ ቴአትር - ሜክሲኮ አደባባይ - አፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ዙሪያ
  • ከፓርላማ መብራት - ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት - ወዳጅነት ፓርክ - ንግድ ማተሚያ ቤት - ሞናርክ ሆቴል - ቴዎድሮስ አደባባይ - ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል - ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን - ብሔራዊ ቴአትር - ሜክሲኮ አደባባይ - አፍሪካ ሕብረት ባሉ መንገዶች እንግዶች ሲያልፉ አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ለእንግዶቹ ቅድሚያ በመስጠት ተባባሪ እንዲሆኑ እና ሌሎች ተለዋጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ፖሊስ አሳስቧል። 

በተጨማሪም፦  

  • ከፓርላማ መብራት - ሸራተን ሆቴል ቁልቁለቱን - ፍልውሃ እና አምባሳደር ቴአትር ዙሪያውን
  • ከንግድ ምክር ቤት ጀምሮ በሱዳን ኤምባሲ - አፍሪካ ሕብረት ዋናው በር - ሳርቤት ድረስ በሁለቱም አቅጣጫዎች ከነገ ሐሙስ የካቲት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እንግዶች ተጠቃለው እስኪመለሱ ድረስ ግራና ቀኝ በሁለቱም አቅጣጫዎች ለአጭርም ሆነ ለረጅም ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። 

ህብረተሰቡ የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘትም ይሁን መረጃ ለመስጠት ሲፈልግ በ011-1-11-01-11፣ 011-5-52-63-03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 መደበኛ የስልክ ቁጥሮች እንዲሁም በ987፣ 991 እና 916 ነፃ የስልክ መስመሮች መጠቀም እንደሚችል የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልፆ፤ ለጉባኤው በሰላም መጠናቀቅ መላው ሠላም ወዳድ ህዝብ ለሚያደርገው ቅን ተባባሪነት አስቀድሞ ምስጋና አቅርቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top