ልጆች አስተዳደጋቸውን እና ትምህርታቸውን ይመስላሉ። ንፁህ የሆነው አዕምሮአቸው የያዘውን አይለቅም፤ የሚያዩትን እና የሚሰሙትን የመያዝ አቅማቸው ከፍ ያለ ነው።
ለዚያም ነው ልጆች መዋዕለ ሕፃናት ውስጥ እያሉ በሁለገብ እውቀት እና ክህሎት እንዲያድጉ ማድረግ የሚመከረው።
ለዚህ ምሳሌ የምትሆነው ቻይና መዋዕለ ሕፃናት ለልጆች ሙያ እና ሥነ-ምግባር ትምህርት አሰጣጥ በተለየ መልኩ ትሰራለች።
በሕፃናት ማቆያዎች የመማር ማስተማር ሂደት ልጆች ልዩ ልዩ ሙያዊ ሥራዎችን እና ምግባሮችን እንዲቀስሙ ይደረጋል።
በዚህም ሕፃናት በ6 ዓመት ዕድሜያቸው አልፎ አልፎም በ3 ዓመታቸው ልብስ መስፋት፣ ምግብ ማብሰል፣ የኮንስትራክሽን ሥራዎች መሥራት፣ ጥልፍ መጥለፍ እንዲሁም ሌሎች ሥራዎችን አቀላጥፎ የመሥራት ብቃት እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል።

እንዲህ ያለው ምግባር በእኛስ ሀገር ለምን በደንብ አልተለመደም የሚል ቁጭት ይፈጥራል::
በአዲስ አበባ የፋሲካ መዋዕለ ሕፃናት ማናጀር ቤተልሔም ከልክላቸው የቻይና መዋዕለ ህጻናት የትምህርት ዘዴ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ እንደሆነ ነው የነገሩን::
ተማሪዎች በፅንሰ-ሐሳብ ብቻ ተምረው ማለፋቸው በቂ አለመሆኑን የነገሩን ማናጀሯ በመዋዕለ ሕፃናት ጅምር ስራዎች ስለመኖራቸው ጠቁመውናል።
"በእኛ ትምህርት ቤት ‘ሞንቶሶሪ’ (በተግባር የሚሰጥ) ዘዴን እንጠቀማለን" የሚሉት ማናጀሯ፣ "ልብስ ማጠፍ፣ የተጠቀሙበትን ዕቃ ማነሣሣት፣ ዕቃዎቻቸውን መለየት እንዲችሉ ይደረጋል"::
በሕይወት ክህሎት የሚጠቅማቸውን ነገሮች እንደሚማሩ እና እንዲተገብሩ እንደሚደረግ ነው የገለጹልን።
ነገር ግን እንደ ቻይና እና ሌሎች ሀገራት የተሟላ የክህሎት ማሠልጠኛ ቁሳቁስ አለመኖሩ እና በደንብ የሠለጠኑ መምህራኖች ስለማይገኙ የምንጠብቀውን ያህል ውጤት ማምጣት አልቻልንም ሲሉ ጠቅሰዋል።
በሀገራችን ልጆች የትምህርት ቤታቸውን የደንብ ልብስ ከመልበስ ጀምሮ ወላጆ ናቸው የሚያደርጉላቸው የሚሉት ማናጀሯ፣ እነዚህ ልምዶች መቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከ3 እስከ 6 ዓመት በልጆች ላይ መሠረት የምንጥልበት ነው ያሉት ማናጀሯ፣ ይህን ባህል ብናመጣ እና ልጆች ላይ በደንብ ቢሠራ ትውልድን መገንባት እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ ቤዛዊት ምንውዬለት እንደምትለው፣ ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ በጨዋታ መልክ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እና ተግባሮች ለዕድገታቸው ወሳኝ ናቸው።
ልጆች በመዋዕለ ሕፃናት ቆይታቸው በጨዋታ መልክ ነገሮችን እንዲረዱ ማድረግ ለአዕምሮ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቅሳለች።
ከዚህ ቀደም በሕፃናት የትምህርት እና ክህሎት ላይ ብዙ ትኩረት አልተሰጠም ያሉን ደግሞ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም አስተባባሪ ታቦር ገ/መድህን (ዶ/ር)፤ ባለፉት 4 እና 5 ዓመታት መንግሥት በልዩ ትኩረት እየሠራበት እንደሚገኝበት ገልጸዋል።
የቀዳማይ ልጅነት መርሐ ግብርም የወላጆች የማማከር አገልግሎት፣ የማኅበራዊ ድጋፍ፣ የመጫወቻ ቦታዎችን መገንባት፣ የሕፃናት እንክብካቤ ማዕከላትን እንደሚያካትት ነው የተናገሩት።
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችን እና ከክፍል ውጪ ያሉ ስፍራዎችን ለልጆች አመቺ ተደርጎ የመሥራት ሥራዎች መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።
ሁሉም የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ እየተሠራ መሆኑን እና ከሁለቱም ዘርፍ ከ14 ሺህ በላይ መምህራን እንዲሁም ሱፐርቫይዘሮች መሠልጠናቸውን አብራርተዋል።
በሜሮን ንብረት