ኢትዮጵያ በአየር ኃይል መስክ ያካሄደቻቸው የለውጥ ተግባራት ከሀገራት ጋር የሚኖራትን ትብብር የሚያሳድግ ነው - ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

10 Mons Ago 824
ኢትዮጵያ በአየር ኃይል መስክ ያካሄደቻቸው የለውጥ ተግባራት ከሀገራት ጋር የሚኖራትን  ትብብር የሚያሳድግ ነው - ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

ኢትዮጵያ በአየር ኃይል መስክ ያካሄደቻቸው የለውጥ ተግባራት በዘርፉ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚኖራትን ትብብር የሚያሳድግ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።

"በመስዋዕትነት ሀገርን የዋጀ የኢትዮጵያ አየር ኃይል" በሚል መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ከኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የአየር ምድቦችና ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል።

የመርኃ-ግብሩ አካል የሆነ የመጀመሪያው የአፍሪካ አየር ኃይል አዛዦች የምክክር መድረክ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል አዛዦች፣ የተለያዩ ሀገራት የአቪዬሽን ተቋማት ኃላፊዎችና ወታደራዊ አታሼዎች በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከምስረታው ጀምሮ አሁን የደረሰበትን ሁለንተናዊ አቅም የሚያሳይ ገለጻ አቅርበዋል።

በገለጻቸውም የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት እና ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች ሀገር መሆኗን አውስተዋል።

በአቬዬሽን ምሥረታ ዘርፍም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ መሆኗን ጠቁመው፤ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተመሠረተ ታሪካዊ አየር ኃይል ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።

አየር ኃይሉ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር መሰማራቱንና በታሪክ የሚወሳ ግዳጅ መፈጸሙን ሌተናል ጄነራሉ አውስተዋል።

የመንግሥታት መቀያየር አየር ኃይሉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ማድረጉን ተናግረው፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በአየር ኃይል በርካታ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

ተቋማዊ ሪፎርም፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ፣ የትጥቅ አቅምን ማዘመን፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታ እንዲሁም የዘርፉን ትምህርት ተቋማት ማቋቋም በአየር ኃይሉ የተከናወኑ አመርቂ የለውጥ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የለውጡ እንቅስቃሴ ለአየር ኃይሉ አዲስ ዘመን የፈጠረ ነው ያሉት ዋና አዛዡ፤ ከቀድሞው በተለየ አዳዲስ ተልዕኮዎችን ለመወጣት አስተማማኝ ቁመና ላይ እንዲገኝ አስችሎታል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ እና አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት የለውጥ ስራ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የሚኖረውን ትብብር የሚያሳድግ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የለውጥ ተግባራት በምሳሌነት የሚነሱ ናቸው ያሉት ዋና አዛዡ፤ አፍሪካውያን ለትብብር ስራ አብረን እንነሳ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top