በሶማሌ ክልል ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

9 Mons Ago
በሶማሌ ክልል ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ ከእቅድ በላይ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

በሶማሌ ክልል በ2014/2015 የምርት ዘመን ከለማው መሬት ከ20 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በመሰብሰብ ከዕቅድ በላይ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ።

በጅግጅጋ ከተማ እየተካሄደ ባለው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ የክልሉን መንግሥት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ከተመለከቱት መካከል የግብርና ስራዎች ክንውን ይገኝበታል።

በ2014/2015 የምርት ዘመን 655 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከለማው መሬት 20 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

ክንውኑ በምርት ዘመኑ 480 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ከታቀደው በላይ እንደሆነ ነው ርዕሰ መስተዳደሩ ያመለከቱት።

ከተሰበሰበው ምርት ውስጥ ስንዴ፣ በቆሎና ማሽላ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከዚህም ሌላ ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ የዕቅዱን 99 በመቶ ማሳካት መቻሉን አስታውቀዋል።

ለ71 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ለ52 ሺህ 919 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ በክልሉ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ በተደረገው ጥረት 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 211 ባለሀብቶችን ማስተናገድ መቻሉን ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።

የሰላምና ፀጥታ ስራን በተቀናጀ መንገድ በመምራት ውጤታማ ስራ መከናወኑን አስረድተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ባለፉት ስድስት ወራት በጤና፣ በትምህርት፣ በእንስሳት ሀብት እና በሌሎች መስኮች የተከናወኑ ስራዎችንም አቅርበዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አያን አብዲ፥ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በመንግስት የተነደፉ የልማት ስራዎች በዕቅዳቸው መሰረት ስለመተግበራቸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሜቴዎች የቁጥጥርና ክትትል ስራ ማካሄዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር በማድረግ በክልሉ የሚካሄዱ የአርብቶ አደር ገጠር ልማት፣ የሠላምና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እንዲጠናከሩ እያስቻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን የያዘው የክልሉ ምክር ቤት ስድስተኛ ዘመን አራተኛ መደበኛ ጉባኤ በርዕሰ መስተዳደሩ በቀረበ የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እየተወያየ መሆኑ ተገልጿል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top