የ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አዘጋጅ የሆነችው ጅግጅጋ በዓሉን ለማድመቅ ደፋ ቀና እያለች ነው

11 Mons Ago 881
የ18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል አዘጋጅ የሆነችው ጅግጅጋ በዓሉን ለማድመቅ ደፋ ቀና እያለች ነው

ዘንድሮ በሶማሌ ክልል የሚከበረውን 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ለማክበር በክልል ደረጃ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ረሺድ ገለፁ።

''ብዝሃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት''በሚል መሪ ቃል ለ18ኛ ጊዜ በሶማሌ ክልል የሚከበረውን በዓል ለማዘጋጀት በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ አብይ ኮሚቴ እና የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ መገባቱን አቶ አብዱልቃድር ረሺድ ተናግረዋል።

ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በጅግጅጋ ከተማ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በተለይ የአዳዲስ መንገዶች፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና የመናፈሻዎች ግንባታ እንዲሁም ከተማዋን የማስዋብ ስራ እየተሰራ መሆኑን አክለው ገልፀዋል።

በተለይም በዓሉን ለመታደም ወደ ክልሉ በተለይ ወደ ጅግጅጋ ከተማ ለሚመጡ እንግዶች የማረፊያ ቦታ እጥረት እንዳያጋጥም ከሆቴሎች በተጨማሪ ሌሎች ማረፊያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን እና ለዚህም የተዋቀረው ኮሚቴ ወደ ስራ መግባቱን ሀላፊው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በዓሉን ከወትሮው በተለየ ብዝሀነትና ኢትዮጵያዊነትን በተላበሰ መልኩ ለማክበር በፌደራል ደረጃ ከተቋቋመውና በፌደሬሽን ምክር ቤት ከሚመራው ኮሚቴ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ሲሆን፣ ለበዓሉ እየተደረገ ያለው ይህ ዝግጅትም በየሳምንቱ በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት  እየተገመገመ ነው ብለዋል።


ተያያዥ ርዕሶች

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top