የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ እውነተኛ የፌደራል ስርዓት ገቢራዊ እንዲሆን እየተሰራ ነው - አቶ አገኘሁ ተሻገር

10 Hrs Ago 60
የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ እውነተኛ የፌደራል ስርዓት ገቢራዊ እንዲሆን እየተሰራ ነው - አቶ አገኘሁ ተሻገር

ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው 19ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የአማራ ክልል የማጠቃለያ መርኃ ግብር በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በ1998 ዓ.ም ሲወሰን ብሔር ብሔረሰቦች ያላቸውን እምቅ ባህል በመለዋወጥና በመተዋወቅ የተሻለ ሀገር እንድትገነባ በማለም ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት ብዝሀነት የልዩነት ምንጭ እንዲሆን ሲቀነቀን ቆይቷል ይሁንና ይህ ትክክል አልነበረም ሲሉም ገልፀዋል፡፡

የሀሳብ ልዕልና እና ስክነት ሀገርን ከአደጋ ይጠብቃል ስለዚህ ሁሉም ህዝብ ይህንን ሊገነዘብ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በመቻቻል የዳበረ የጋራ አብሮነት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ስለሚያግዝ በዚህ ላይ መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የለውጡ መንግስት ከመጣ በኋላ እውነተኛ የፌደራል ስርዓት ገቢራዊ እንዲሆን እየተሰራ ነው ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለዚህም የሚያግዝ እና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚገነቡ ስራዎች እየተከናወኑ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ልታድግ እና ልትበለጽግ የምትችለው የሚታዩ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው እና የጋራ ትርክቶች ላይ የበለጠ ትኩረት በማድረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል እየታየ ያለው ፍላጎትን በኃይል ለማሳካት እየተደረገ ያለው ጥረት ህዝቡንም ሀገርንም ዋጋ እያስከፈለ ነው ያሉት አቶ አገኘሁ፤ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የፌደራል እና የክልሉ መንግስት በሩ ክፍት ነው ብለዋል፡፡

በዮሃንስ ፍስሃ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top