የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሳኡዲ አረቢያ የንግድ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ሙሀመድ ቢን ሙጃብ አል- ሁዋይዚ እና ከሳዑዲ የውጭ ንግድ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት፤ በአዲስ አበባ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያ የቢዝነስ ፎረም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ለማጠናከር መሰረት የጣለ ነው።
ኢትዮጵያ እየተገበረች የሚገኘው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።
የሳዑዲ ባለሃብቶችም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሠማሩ ጥሪ አድርገውላቸዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የሳኡዲ ልዑካን ቡድን አባላት ጉብኝቱ የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ጥንካሬ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሳዑዲ ንግድ ድርጅቶችና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን መልካም ዕድል በመጠቀም በግብርና፣ በማዕድን እና በሌሎችም ዘርፎች እንዲሰማሩ እንደሚደግፉ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።