በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እናት እና ልጅ አንድ ላይ የተመረቁበት አጋጣሚ

3 Mons Ago 484
በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ እናት እና ልጅ አንድ ላይ የተመረቁበት አጋጣሚ

የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛና መጀመሪያ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች አሰልጥኖ ትናንት ካስመረቃቸው 1 ሺህ 589 ተማሪዎች መካከል እናትና ልጅ ተመራቂዎች ክስተት ናቸው።

ሲስተር ገነት ሐጎስ በስነ ተዋልዶ ጤና በሁለተኛ ዲግሪ በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ሲሆን፣ ሶስተኛ ልጃቸው የሆነው ወጣት ያሬድ ካሳ ደግሞ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ነው።

“የትምህርት ፍላጎት ካለ የማይቻልና የማይደረስበት ስኬት የለም” ያሉት ሲስተር ገነት ወደ ዩኒቨርስቲው ለማስመረቅና ለመመረቅ መምጣታቸው ለቤተሰባቸው ኩራት፣ ለተመራቂ ተማሪዎች ድምቀት፣ ለወላጆች ደግሞ ጥንካሬን በተግባር ያሳየ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

ከኔ ጋር የተመረቀው ሶስተኛ ልጄን ሳይጨምር ሌሎች ሁለት ልጆቼን አስተምሬ ለቁም ነገር አድርሻለሁ ያሉት ሲስተር ገነት፣ በጤናው ዘርፍ ከ20 ዓመት በላይ ህዝባቸውን በቅንነትና ታማኝነት ማገልገላቸውን አውስተዋል።

ዛሬም በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሙያቸው እያገለገሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከልጅነታቸው ጀምረው ለትምህርት ልዩ ትኩረት ይሰጡ እንደነበርና በየደረጃው በሚገኙ የትምህርት ደረጃዎች የላቀ ውጤት በማምጣት የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ እንደነበር ያስታወሱት ሲስተር ገነት፤ በተማሩት የሁለተኛ ዲግሪ በከፍተኛ ማእርግ ከመሸለም ዕድሜ እንዳላገዳቸው ተናግረዋል።

ቤተሰብ እያስተዳደሩና በጤናው ዘርፍ ህዝባቸውን እያገለገሉ በዩኒቨርስቲ ትምህርት መከታተልና ለውጤት መብቃት ቀላል አይደለም ያሉት ሲስተር ገነት፣ ፍላጎት ካለ የማይቻል ነገር የለም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀው ያሬድ ካሳ በበኩሉ እናቴ ለኔ ተምሳሌቴ ናት፤ በህይወት ዘመኔ ፅናትና የይቻላል መንፈስ እንድወርስ አድርጋኛለች ብሏል።

በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ሁሌም የእናቱን ጥንካሬ እያስታወሰ በርትቶ ለመማር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለት መቆየቱን አስታውሷል።

ትምህርት መማር የእድሜ ገደብ እንደሌለው ከእናቴ በቅርብ ተምሬያለሁ ያለው ተመራቂ ያሬድ፣ እንደ እናቱ የተሳካ ህይወት እንዲኖረው ፍላጎቱ መሆኑን ገልጿል።

እናትና ልጅ ተመራቂዎች ለዚህ እድል የበቁት ሰላም በመገኘቱ መሆኑን ገልጸው፤      ሰላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ እጅጉን ልንንከባከበው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወጥቶ ለመግባት፣ ሰርቶ መኖርና ተምሮ መመረቅ ሰላም ሲኖር ነው የሚሉት እናትና ልጅ ፣ ከቤተሰብ ጀምሮ ሁሉም ለሰላም ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top