ሩስያ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ስትራቴጂክ ትብብር ያጠናክራል ያለችውን የአፍሪካ የትብብር ቢሮ (Department for African Partnership) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ከፍታ ሥራ ጀምራለች።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በሩሲያ ፌዴሬሽን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ገነት ተሾመ (ዶ/ር) ጨምሮ የአፍሪካ አምባሳደሮች ተገኝተዋል።
በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ በተከፈተው የአፍሪካ የትብብር ዲፓርትመንት (Department for African Partnership) ቢሮ ትውውቅ ፕሮግራም ላይ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ አዲሱ ቢሮ በሩሲያ እና አፍሪካ መካከል ያለው ስትራቴጂክ አጋርነት የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል።
በሩሲያ እና አፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር ልዩ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
ከሶቪየት ሕብረት ጊዜ ጀምሮ አፍሪካ በፀረ-ኮሎንያሊዝም ትግል አገራቸው የነበራትን ጠንካራ ድጋፍ ያስታውሰት ላቭሮቭ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን በመዋጋት የአፍሪካ ሕብረት መርህ ተግባራዊ እንዲሆን ሩሲያ አስተዋጽኦ ማድረጓን ገልፀዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ ላይም አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ሀገራቸው ድጋፏን እንደምትቀጥል ሚንስትሩ አረጋግጠዋል።
በሩሲያ-አፍሪካ ፎረም እንዲሁም እስካሁን በሩሲያ እና አፍሪካ አገራት መካከል የተፈረሙ የጋራ ስምምነቶች የትምህርት እድል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የንግድ ግንኙነት ላይ አዲሱ ቢሮ ብዙ ስራዎችን እንደሚሰራ ላቭሮቭ ጠቅሰዋል።
የአዲሱ ቢሮ ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ታታያና ዶቭጋሌንኮ በበኩላቸው በአፍሪካና ሩስያ መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ለመወጣት ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰሩ ሶስት ቢሮዎች ማለትም (ከሰሃራ በታች አፍሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና ሰሜን አፍሪካ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ፓርትነርሺፕ) ሆነው መዋቀራቸውንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በሩሲያ እና አፍሪካ መካከል የነበሩት ታሪካዊ ግንኙነቶች፣ የፓን አፍሪካ አባቶች በሞስኮ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች እና የሩሲያ-አፍሪካ ፎረምን የሚያሳዩ የፎቶ ኤግዚቢሽን ክፍት ተደርጓል።