የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያና የመዝናኛ ስፍራ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

1 Mon Ago 344
የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያና የመዝናኛ ስፍራ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

በአዲስ አበባ አራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያ እና የመዝናኛ ስፍራ በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በመዲናዋ በኮሪደር ልማት የተገነቡ መሰረተ ልማቶችና የመዝናኛ ስፍራዎች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ።

ከእነዚህ የልማት ሥራዎች አንዱ የሆነው የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያ እና መዝናኛ ስፍራ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ዛሬ በይፋ ወደ አገልግሎት ገብቷል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ከተማዋን ውብ፣ ጹዱና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ዛሬ ለምረቃ የበቃው የአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያና መዝናኛ ስፍራ ፋይዳው የላቀ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አካባቢው ከዚህ ቀደም ለተሽከርካሪ፣ ለእግረኞችና ለአካል ጉዳተኞች መተላለፊያነት አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ችግሩን በሚቀርፍና ዘመናዊነቱን በጠበቀ መልኩ መገንባቱን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አካል ጉዳተኞችም በቀላሉ መተላለፍ የሚችሉበት የአሳንስር መጓጓዣ መኖሩንም ነው የተናገሩት።

በውስጡ የሀገር ውስጥ አልባሳት፣ መዋቢያዎች፣ ወርቅና ብር መሸጫ ቤቶች፣ የስልክ መሸጫዎች፣ የፈጣን ምግብ አገልግሎት እና መሰል የንግድ አገልግሎቶች መጀመራቸውንም ተናግረዋል።

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top