የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡- ፕሮፌሰር አለማየሁ ተክለማርያም

4 Days Ago 456
የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡- ፕሮፌሰር አለማየሁ ተክለማርያም
ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ባህሪ ጥናት ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተክለማርያም ገልጸዋል።
 
97 አንቀጾችን የያዘው የአጠቃላይ ትምህርት አዋጁ፣ ምን ምን ማሻሻያዎችን በውስጡ ይዟል የሚለውን ጉዳይ ኢቲቪ በአዲስ ቀን 'የሀገር ጉዳይ' መሰናዶው ተመልክቶታል፡፡
 
በኢትዮጵያ ያለውን የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ አዋጁ አስገዳጅነት ያለው፣ አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የሚያደርግ መሆኑንም ፕሮፌሰር አለማየሁ ተክለማርያም ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ ያለው ቁልፍ የትምህርት ጥራት ችግር የመምህራን ጥራት መሆኑን በመገንዘብ መምህራን በሙያቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሰለጥኑ በአዋጁ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ ያሉ 90 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኞች ወደ ትምህርት ቤት አለመሄዳቸውን ታሳቢ በማድረግ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ አዋጁ እንደሚያስገድድ ፕሮፌሰር አለማየሁ ተናግረዋል፡፡
 
ሥርዓተ ትምህርት በየጊዜው እንደሚሻሻል በጸደቀው አዋጅ ውስጥ መካተቱን የገለጹት ፕሮፌሰሩ፤ የሥርዓተ ትምህርት መሻሻል ለትምህርት ጥራት አንደኛው ነገር ነው ብለዋል፡፡
 
ተማሪዎች ቢያንስ 3 ቋንቋዎችን እንዲማሩ እና አፈፃፀሙም በክልሎች የሚወሰን ሲሆን አንድ ተጨማሪ የሀገር ውስጥ ቋንቋ ከፌደራል የስራ ቋንቋዎች መካከል የተማሪ ወይም ወላጆች ምርጫን ታሳቢ አድርጎ ይሰጣል የሚል በአዋጁ ተካቷል፤ ይህም የተማሪዎችን አስተውሎት የሚጨምር በመሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።
 
በተለያዩ ቋንቋዎች ትምህርት እንዲሰጥ መወሰኑ ተማሪዎች ከራሳቸው አልፈው የሌላውን ባሕልና ታሪክ እንዲያውቁ እንደሚረዳቸው ነው የገለጹት፡፡
 
አዋጁ መውጣቱን ተከትሎ የግል ትምህርት ቤቶች የመንግስት ትምህርት ቤቶች ከሚሰጠው ጋር ወጥና ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ትምህርት የሚሰጡበት አሰራር ይዘረጋል ተብሏል ፡፡
 
አዋጁ የግል ትምህርት ተቋማት ከመንግሥት ሥርዓተ ትምህርት ሳይወጡ ተወዳዳሪ መሆን የሚችሉበት ስለመሆኑም ነው ፕሮፌሰር አለማየሁ የተናገሩት።
 
የአዋጁን ተፈጻሚነት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ አዲሱን አዋጅ ለመተግበር የሽግግር ሂደት በመሆኑ የነበረውንና አዲሱን አዋጅ ጎን ለጎን ማስኬድ ሊያስፈልግ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
 
የአጠቃላይ ትምህርት አዋጁ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲያስችል ቁርጠኛ አፈፃፀም እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ለተግባራዊነቱ ሁሉም መረባረብ አለበት ብለዋል፡፡
 
በመሐመድ ፊጣሞ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top