የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ጋዛን በጊዜያዊነት ተቆጣጥራ ፍልስጤማውያንን መልሳ ማስፈር እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር በዋይት ሃውስ በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መገለጫ እንዳሉት፤ አሜሪካ በጋዛ የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማስወገድና ኢኮኖሚዋን በማሳደግ የፍልስጤምን ግዛት "የመካከለኛው ምሥራቅ ሪቪያ" የማድረግ ሥራ መሥራት እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡
መልሶ ግንባታው ሲካሄድም ፍልስጤማውያን ከጋዛ ውጭ እንዲሰፍሩ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህ ሀሳብ ከዚህ ቀደም ተነስቶ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ሁሉም ሀገራት እንዳልተቀበሉት ተጠቅሷል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ነጩ ቤተመንግሥት ከተመለሱ በኋላ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው የውጭ ሀገር መሪ የሆኑት ኔታንያሁ፣ የትራምፕ እቅድ "ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ" ሀሳብ ነው ብለዋል፡፡
የቢቢሲው የዲፕሎማሲ ጋዜጠኛ ፖል አዳምስ ፕሬዚደንት ትራምፕ ስለጋዛ ያቀረቧቸው ሃሳቦች የብዙዎችን ቀልብ የሳቡ እና አስደንጋጭ ናቸው ሲል ገልጿቸዋል።
በተመድ የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ ማንሱር ሕዝባቸውን ወደ ጋዛ መመለስ እንደሚፈልጉ ሲናገሩ፣ ሃማስ ደግሞ የትራምፕን እቅድ ቅዠት ነው ማለቱን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡