አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው ከኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ የሹመት ደብዳቤ እና የሥራ መመሪያ ተቀብለዋል።
ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀ ሥላሴ በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያና አሜሪካ ከ120 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆኖ መሾም የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ኃላፊነትና አደራ መጎናጸፍ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የረጅም ዘመን ግንኙነትን የሚያጠናክር ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባት ሀገር በመሆኗ በኢትዮጵያ ልማትና እድገት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አምባሳደሩ ጠንካራ ስራ ማከናወን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
በመሆኑም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም፣ አሜሪካ ትልቅ እሳቤን የሚጠይቅ ዲፕሎማሲ የሚከናወንባት መሆኑን ታሳቢ ያደረገ አመራር እንዲሰጡም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ወዳጅን ማብዛት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በቀጣናው ሰላምና ትብብርን ለመፍጠር ጠንካራ ዲፕሎማሲ እና የውጭ ግንኙነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለጀመረችው የፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ውጤታማነት ከአሜሪካ ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በቀጣይ በሰላም፣ በጸጥታና በዳያስፖራ ጉዳዮች ዙሪያ ያቀደቻቸውን ግቦች ለማሳካት አምባሳደር ብናልፍ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት አማካኝነት ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።